ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ህገወጥ የይዞታ ካሳ ክፍያ ወስደዋል የተባሉ ተከሳሾች ከ19 እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦሌ አራብሳ ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ህገወጥ የይዞታ ካሳ ክፍያ ወስደዋል ተብለው የተከሰሱ 19 ተከሳሾች ከ19 እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነ።
የቅጣት ውሳኔውን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቢ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በየካቲት 30 ቀን 2014 ዓ.ም የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶ ነበር።
በቀረበባቸው ክስ ላይ እንደተመላከተው ቦሌ አራብሳ አካባቢ በውሃና ፍሳሽ ተቋም ለሚገነባው ውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት ስራ ይዞታ ከሌላቸው 21 ግለሰቦች ጋር በዝምድና እና በጥቅም በመተሳሰር የመሬት ይዞታ እንዳላቸው ተደርጎ ስም ዝርዝር በማስገባትና በይዞታ ባለቤትነት በሀሰት ለተመዘገቡ ቤተሰብና የተለያዩ ግለሰቦች ውክልና በመውሰድ ይዞታ በማረጋገጥ፣ የይዞታ ካሳ በማጽደቅና እንዲሁም ከህግ ውጪ ከ65 ሚሊየን ብር በላይ የይዞታ ካሳ ክፍያ ገንዘብ በተለያዩ መጠኖች በ2013 ዓ.ም መጨረሻ በተለያዩ ቀናቶች መውሰዳቸው ተጠቅሷል።
ክስ ቀርቦባቸው ከነበሩ ከአጠቃላይ 21 ተከሳሾች ውስጥ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ገረመው ይገዙን ጨምሮ 16 ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተከሳሾች መሆናቸውን ተከትሎ ችሎቱ በተደጋጋሚ ቀጠሮ ሊቀርቡ ባለመቻላቸው እና ፖሊስ በአድራሻቸው አላገኘኋቸው የሚል መልስ በመስጠቱ በመጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በነበረ ቀጠሮ በሌሉበት መዝገቡ እንዲቀጥል ብይን ተሰጥቶ ነበር።
ቀሪዎቹ ግን ማለትም የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች የሆኑት አቶ በቀለ ገረሱ፣ ጫላ አለሙ፣ ተስፋዬ አለሙ እንዲሁም የክፍለ ከተማው የካሳ መረጃ አሰባሳቢ ባለሙያዎች ናቸው የተባሉት ገዛኸኝ አንቦ እና አብርሐም አለነ ክስ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ክሱ ደርሷቸው ጉዳያቸውን ተከታትለዋል።
ዐቃቤ ሕግ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ላይ ከስድስት በላይ ምስክሮችን እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በተለያዩ ቀናቶች አሰምቷል፤ ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሯል።
በዚህም በከባድ ሙስና ወንጀል የተከሰሱት የወረዳ 6 ስራ አስፈጻሚ ገረመው ግዛቸውን ጨምሮ 16 ተከሳሾች ላይ በሌሉበት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።
ቀሪ ሌሎች 5 ተከሳሾች የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች የሆኑት አቶ በቀለ ገረሱ፣ ጫላ አለሙ፣ ተስፋዬ አለሙ እንዲሁም የክፍለ ከተማው የካሳ መረጃ አሰባሳቢ ባለሙያዎች ናቸው የተባሉት ገዛኸኝ አንቦ እና አብርሐም አለነ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶባቸው ነበር።
ተከሳሾቹ በተለያዩ ቀናቶች ያቀረቡትን የመከላከያ ማስረጃን የመረመረውፍርድ ቤቱ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሽ የነበሩት ገዛኸኝ አንቦ እና አብርሐም አለነ የተባሉ ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው መከላከላቸውን ገልጾ በነጻ አሰናብቷቸዋል።
በማረሚያ ቤት የሚገኙትን በቀለ ገረሱ፣ ጫላ አለሙ እና ተስፋዬ አለሙ በሚመለከት የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው አልተከላከሉም በማለት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።
ዛሬ በዋለው ችሎት ደግሞ ፍርድ ቤቱ ከማረሚያ ቤት የቀረቡትን 14ኛ ተከሳሽ በቀለ ገረሱ፣ 15ኛ ተከሳሽ ጫላ አለሙ እና 19 ተከሳሽ ተስፋዬ አለሙን በሚመለከት ስድስት፣ ስድስት የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ በመካከለኛ የወንጀል ደረጃ እያንዳንዳቸውን በ12 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
በሌሉበት ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾችን በተመለከተ ማለትም 1ኛ ተከሳሽ የወረዳ 6 ስራ አስፈጻሚ የነበሩትን አቶ ገረመው ይገዙን በ12 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ 9ኛ ተከሳሽ መልካሙ አካሉን በ18 ዓመት ጽኑ እስራትና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ የተወሰነ ሲሆን 16ኛ እና 18ኛ ተከሳሾች ማለትም ወንድሰን ጫላና አሸናፊ ዲባባን ደግሞ በ19 ዓመት ጽኑ እስራትና በ50 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
የተቀሩ ተከሳሾችንም በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በ12 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።
ፍርድ ቤቱ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የዕስራት ቅጣቱን እንዲያስፈጽም አዟል።
ያልተያዙት 16 ተከሳሾችን ደግሞ ፖሊስ አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ