ሌ/ጄ ሹማ አብደታ በግዳጅ ላይ የሚገኙ የሠራዊት አባላትን አበረታቱ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ እና የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ዋና ሰብሳቢ ሌ/ጄ ሹማ አብደታ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የክፍሉን የሠራዊት አባላት በግዳጅ ቀጠናቸው ተገኝተው አበረታትተዋል፡፡
ሌ/ጄ ሹማ አብደታ በጉብኝታቸው ወቅታዊ የሀገሪቱን ሁኔታ በማንሳት ለሰራዊቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዓለም ላይ የበርካታ ሀገራት ዜጎች በሰላም እጦት ሀገር አልባ በመሆን የደረሰባቸውን ችግር አንስተውም ገለጻ አድርገዋል፡፡
በአማራ ክልል ጽንፈኛው ኃይል እና በኦሮሚያ ክልል አሸባሪው ሸኔ የኢትዮጵያን ህዝቦች በተመሳሳይ መልኩ ሀገር አልባ ለማድረግ የሚሞክሩት ሴራ ፈፅሞ አይሳካም ብለዋል።
ሁለቱም ፀረ ሰላም ሃይሎች በአሁኑ ወቅት በሠራዊቱ ምት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸው መዳከማቸውን እና አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን በመግለፅ÷ ለተገኘው ውጤት ለሠራዊቱ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡
ልክ እንደ አባቶቹ ከባንዳዎች አፍ ነጥቆ የታፈረች እና የተከበረች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው ሠራዊት ህዝቡና መንግስት ታላቅ ክብር እንዳለውም አሥረድተዋል።
ሁለቱ ፅንፈኛ ሃይሎች እርስ በርሳቸው እንኳን የማይታረቅ ሀሳብን ይዘው በህዝብ ላይ ያደረሱት በደልና ሰቆቃ ቀላል የማይባል መሆኑን ሌተናል ጄነራሉ ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ላይ በሠራዊቱ ብርታት ሁኔታዎች እየተሻሻሉ እንደሚገኙ መግለጻቸውንም የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡