ኢትዮጵያ በአፍሪካ-ቱርክ ግንኙነት መድረክ ላይ ተሳተፈች
አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቱክር የኢትዮጵያ አምባሳደር አደም መሐመድ በአፍሪካ-ቱርክ ግንኙነት የውይይት መድረክ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የውይይት መድረኩን አንካራ ሐጂ ባይራም ቬሊ ዩኒቨርሲቲ ከቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ነው በጋራ ያዘጋጁት፡፡
በመድረኩ በቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ዳ/ጄኔራል፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፣ በአንካራ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች ቡድን ዲን ጨምሮ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ተሳትፈዋል፡፡
በዚህም የአፍሪካ እና ቱርክ ግንኙነትን አስመልክቶ የፓናል ውይይት መካሄዱን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ስልጣኔ ትግበራ እና ምርምር ተቋም ኃላፊ ዩኑስ ቱርሃን (ረ/ፕ/ር)÷ ኢትዮጵያ ለቱርክ- አፍሪካ ግንኙነት ፈር ቀዳጅ ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡
ቱርክ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ኤምባሲ የከፈተችው በኢትዮጵያ መሆኑን ጠቁመው÷ የቱርክ አባት የሚባሉት ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር የነበራቸውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አስታውሰዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው አንካራ ከሚገኘው የኢፌዴሪ ኤምባሲ ጋር በመነጋገር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ዝግጅት ላይ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡