Fana: At a Speed of Life!

ከባንክ መመሪያና አሰራር ውጭ ከደንበኛ ሂሳብ ገንዘብ እንዲመዘበር አድርገዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2016 (ኤ ፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መመሪያና የአሰራር ስርዓትን በመጣስ ከደንበኛ ሂሳብ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማዘዝ ገንዘቡ እንዲመዘበር አድርገዋል የተባሉ 5 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች 1ኛ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተፈራ ደግፌ ቅርንጫፍ ተጠባባቂ ተቀዳሚ ቅርንጫፍ ባንኪንግ መኮንን በረከት ሙሉ ሃለፎም፣ 2ኛ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተፈራ ደግፌ ቅርንጫፍ ተጠባባቂ የውስጥ ተቆጣጣሪ ማርታ ሃይሉ ምንዳሁን፣ 3ኛ በንግድ ስራ ላይ ይተዳደራል የተባለው ተስፋ ገ/ስላሴ ከበደ ፣ 4ኛ ጌትነት አለማየሁ ይመር እና 5ኛ ሪያን ሰይድ ከድር ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ባቀረበው በአንደኛው ክስ ላይ በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ ያቀረበ ሲሆን፥ በሁለተኛው ክስ ደግሞ ከ3ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ ተከሳሾች ላይ መስርቷል።

በአንደኛው ክስ ላይ እንደተመላከተው 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ያጸደቀው የቅርንጫፍ ባንኮች የአሰራር ስርዓት መመሪያ ደንብን በመተላለፍ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአንድነት ቅርንጫፍ ደንበኛ የሆኑት የግል ተበዳይ አቶ ይትባረክ ይኩኖአምላክ ከሂሳብ ቁጥራቸው ላይ ገንዘብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ሌላ ሰው ሂሳብ እንዲተላለፍ ምንም አይነት ጥያቄ ባላቀረቡበት ሁኔታ ላይ ሁለቱም ተከሳሾች ከደንበኛው ሂሳብ ያለአግባብ ገንዘብ ዝውውር ለመፈፀም እንዲያስችላቸው በባንኩ ተጥሎ የነበረውን የክልከላ ገደብ መተላለፋቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ 1ኛ ተከሳሽ በባንኩ የተሰጠውን ዩዘር ለ2ኛ ተከሳሽ አሳልፎ በመስጠት 2ኛ ተከሳሽም በራሷ ኮምፒውተር የ1ኛ ተከሳሽን ዩዘር በመጠቀም የተነሳውን ክልከላ ያፀደቀች መሆኑ በክሱ ተጠቅሷል።

መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ 2ኛ ተከሳሽ ምንም አይነት ግብይት በሌለበት ሁኔታ የዐቃቤ ህግ 6ኛ እና 7ኛ ምስክሮችን ኮምፒውተር በመጠቀም የደንበኛው የቀሪ ሂሳብ እና ፊርማ ምልከታ በማድረግ ፎቶ በማንሳት መረጃውን አሳልፋ ለሌላ አሳልፋ መስጠቷ ተገልጿል።

መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም ለጊዜው ማንነቱ ያልታወቀ ግለሰብ ከቅርንጫፍ ባንክ ቤቱ ውጪ የተዘጋጁ እና በግል ተበዳይ ያልተፈረሙ ሁለት በሐዋላ ገንዘብ መላኪያ ቅጽ ይዞ በመምጣት ለ1ኛ ተከሳሽ የሰጠው ሲሆን፥ ተከሳሹም 4ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር ደንበኞች እያስተናገደች የነበረችበትን ኮምፒውተር በመጠቀም ለ3ኛ ተከሳሽ በሂሳብ ቁጥር ብር 3 ሚሊየን 240 ሺህ ብር እና ለ4ኛ ተከሳሽ ደግሞ 2 ሚሊየን 160 ሺህ ብር በአጠቃላይ 5 ሚሊየን 400 ሺህ ብር ዝውውር ከፈፀመ በኋላ በራሱ የኮምፒውተር መጠቀሚያ ዩዘር ግብይቶችን ያፀደቀ መሆኑ በክሱ ተዘርዝሯል።

2ኛ ተከሳሽ ደግሞ ግብይቶችን ኦዲት በማድረግ ያረጋገጠች በመሆኑ በአጠቃላይ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የአሰራር ስርዓት መመሪያ በግልጽ ተግባር በመተላለፍ ደንበኛው ባልቀረቡበትና የክፍያ ጥያቄ ባላቀረቡበት ሁኔታ ላይ ከደንበኛ ሂሳብ ውስጥ ያለአግባብ 5 ሚሊየን 400 ሺህ ብር ገንዘብ ወጪ በማድረግ በባንኩ ላይ በዚሁ መጠን ጉዳት እንዲደርስ እና ለሌሎች ሰዎች ያልተገባ ጥቅም እንዲውል ያደረጉ መሆናቸው ተጠቅሶ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በስልጣን አለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በሁለተኛው ክስ ደግሞ ከ3ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ላይ በቀረበው ክስ እንደተገለጸው ተከሳሾች የንብረቱን ህገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ እና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድነት ቅርንጫፍ ደንበኛ ከሆኑት የግል ተበዳይ አቶ ይትባረክ ይኩኖአምላክ ከሂሳብ ቁጥራቸው ላይ ያለአግባብ ውጪ ከሆነው 5 ሚሊየን 400 ሺህ ብር ውስጥ በተለያዩ መጠኖች በተከፈተ ሒሳብ በማስተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ዐቃቤ ህግ አያይዞ አቅርቧል።

ከተከሳሾቹ ውስጥ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጎ ለፊታችን ሰኞ ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.