Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የጋራ ግብረ ኃይሉ አስታወቀ

 

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 8 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ፡፡

በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት ተሳታፊዎች ፣ አምባሳደሮች ፣ ተጋባዥ አትሌቶች የሚታደሙበት መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያዘጋጀው የሩጫ ውድድር ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡

ውድድሩ በሰላም እንዲጠናቀቅ ግብረ ኃይሉ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከውድድሩ ዓላማ ውጪ የሆኑ ህገ-ወጥ ተግባራትንና መልዕክቶችን በልዩ ልዩ ሁኔታ ማስተላለፍ እንዲሁም የተከለከሉና ህጋዊ እውቅና የሌላቸው ባንዲራዎችን፣ ቁሣቁሶችን ወደ ውድድሩ ቦታ ይዞ መምጣት ፈፅሞ የተከለከለና በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑን ገልጿል፡፡

በዚህም የውድድሩ ተሳታፊዎች በመገንዘብ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ግብረ ሀይሉ አሳስቦ ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ እንደሚኖር በመገንዘብ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቋል፡፡

የወድድሩ ተሳታፊዎች እና ተወዳዳሪዎች በሚያልፉት አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪውን ያስተላለፈው የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ህብረተሰቡ ለፀጥታው ስራ ስኬታማነት እያደረገ ላለው ቀና ትብብር ምስጋና አቅርቧል፡፡

ጥቆማ ለመስጠት ይሁን የፖሊስ አገልግሎትን ለማግኘት በስልክ ቁጥር 011-5-52-63-03፣ 011-5-52-40-77፣ 0115-52-63-02፣011-1-11-01-11 ወይም በነፃ ስልክ መስመር 991 እና 987 መጠቀም እንደሚችላም አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.