Fana: At a Speed of Life!

ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር እንሠራለን – የስፔን አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር እንሠራለን ሲሉ በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር ማኑኤል ሳላዛር ተናገሩ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በኢትዮጵያ የስፔን አምባሳደር ማኑኤል ሳላዛር ጋር በሁለትዮሽ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹ ሁኔታ፣ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረትና እንደሀገር ያለውን ዕምቅ የተፈጥሮ ሐብት አቶ መላኩ አብራርተዋል፡፡

የስፔን ባለሐብቶችም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ እንዲሰማሩ ግብዣ አቅርበዋል፡፡

አምባሳደር ማኑኤል ሳላዛር በበኩላቸው÷  መንግሥታቸው የስፔንና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ባለሐብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲሰማሩ ይሠራል ብለዋል፡፡

ስፔን በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ለአፍሪካ ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸው÷  በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነትም በይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እንደምትሠራ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ፀጋና ለኢንቨስትመንት ያላትን ምቹነት ባለሐብቱ እንዲረዳ የሚያስችል መድረክ በጋራ ለማዘጋጀት በውይይቱ ወቅት ስምምነት ላይ መደረሱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.