የጭንቀት መነሻዎችና መፍትሄዎች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ 2019 ባደረገው ጥናት በዓለም ዙሪያ 301 ሚሊየን ሰዎች በጭንቀት ውስጥ እንደሚኖሩ ገልጿል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 58 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ህጻናት እና ወጣቶች መሆናቸውንም ነው የገለጸው።
የአዕምሮ በሽታ ተብለው ከሚጠቀሱና በማህበረሰቡ በስፋት ከሚስተዋሉት መካከል ጭንቀት አንዱ ሲሆን ፥ ከራስ ጋር እና ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖር ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ጫናን ሊፈጥር ብሎም የስራ ምርታማነትን እና ወደስኬት የሚደረገው ጉዞ ላይ እክል ሊፈጥር ይችላል፡፡
ይህም የተወሰነ የእድሜ ክልልን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍልን የሚያጠቃ ነው ይላሉ የዘርፉ ተመራማሪዎች፡፡
የሥነ-ልቦና ባለሙያው ቴዎድሮስ ድልነሳው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታም፥ ያለበቂ ምክንያት ወይም ሊያስጨንቅዎት የሚገባው ነገር ካለፈ በኋላ ስሜቱ ሲቀጥል ጭንቀት እንደሚባል ያስረዳሉ።
በአሁኑ ወቅት መረጃ ከመጠን በላይ መገኘት በራሱ፣ ያለአግባብ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፣ ራስን ከሌሎች ሰዎች ጋር ማወዳደር፣ ጤና፣ ገንዘብ፣ የቤተሰብ ሁኔታ፣ የልጅነት ገጠመኞች፣ ከባድ አጋጣሚዎች፣ ለነገሩ የሚሰጡት ክብደት መጨመሩ እና ሌሎች የጭንቀት መንስዔዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
አብዛኞቹ የአዕምሮ በሽታዎች ያሉበት ደረጃ ባሕርያትና ሁኔታ ከሰውሰው ይለያያሉ የሚሉት የሥነ ልቦና ባለሙያው፥ አንዳንዶቹ ላይ ቀለል ያለ ሌሎች ላይ ደግሞ ከባድ ወይም ውስብስብ ምልክቶችን እንደሚያሳይም ነው የሚናገሩት።
የባህሪ መቀያየር እስከ ማህበራዊ ህይወት መገለል ያሉ ምልክቶች ሊታዩ እንደሚችሉም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የእጅ መንቀጥቀጥ፣ ላብ ላብ ማለት፣ የልብ ምት መጨመር፣ የድካም ስሜት፣ የራስ ምታት፣ የተወሰኑ ነገሮች ላይ ደጋግሞ ማሰብ፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ ደስታ ወይም ፍላጎት ማጣት ምልክቶች እንደሆኑም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
በአብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ሰዎች የሥነ-አዕምሮ በሽታ ተጠቂዎች እንደሆኑ አምነው ወደ ህክምና ተቋም ሄዶ መታከም አልተለመደም ፤ ይህንን ተከትሎም በሽታው ከነበረበት ወደከፍተኛ ደረጃ በመድረስ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም ነው የሚያነሱት።
የአዕምሮ ጤና ጉዳይ ከጊዜ ወደጊዜ አሳሳቢ ወደሆነ ደረጃ ተሸጋግሯል ይላሉ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን፡፡
በአካባቢና በህይወትዎ የሚፈጠሩ ክስተቶች በአግባቡ ካልተቆጣጠሩት እና ራስዎ ላይ ትኩረት አድርገው ካልሰሩ የአዕምሮ ቀውስ ውስጥ ሊከትል ይችላል፡፡
አልፎ አልፎ ጭንቀትን በተለመደው የህይወት እንቅስቃሴ ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ሊያጋጥም እንደሚችልም ነው የሚያስረዱት።
ሆኖም በጭንቀት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በራሳቸው ጥረትና በህክምና ባለሙያዎች እገዛ ተደርጎላቸው መዳን ይችላሉ፡፡
በዚህም ለራስ ጊዜ በመስጠት (በጥሞና) ነገሮችን ማሰላሰል፣ ተረጋግቶ የራስን ህይወት በትኩረት ማየት፣ አስተሳሰብ ላይ ረዘም ያለ ጊዜ በመውሰድ ፍተሻ ማድረግ፣ ለነገሮች የሚሰጡትን አመክንዮ እና ራስ ላይ በማተኮር መፍትሄ መስጠት እንደሚቻል የሥነ ልቦና ባለሙያው መክረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ባስ ካለ ወይም የባለሙያ እገዛ ካስፈለግዎ ሃኪምን ማማከር እንሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
#health #anxiety
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!