አመራሩ የሕዝቡን እርካታ በሚያረጋግጥ ሁኔታ ውጤት ለማምጣት መትጋት አለበት – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በጎንደር የስልጠና ማዕከል ተገኝተው የስልጠናውን ሒደት ተመልክተዋል።
አቶ አደም በዚህ ወቅት ÷ሰልጣኞች በስልጠናው የሚያገኙትን ግብዓት ተግባራዊ በማድረግ የሕዝቡን እርካታ በሚያረጋግጥ ሁኔታ መትጋት አለባቸው ብለዋል፡፡
በተለይም በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ይበልጥ ውጤት ለማምጣት እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡
ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ጉዞን ለማፋጠን ሀገራዊ ራዕይን በአግባቡ መገንዘብና ለተግባራዊነቱ መረባረብ እንደሚገባ መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የውስጠ ፓርቲ አንድነትን ማጠናከርና ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር ለቀጣይ ስኬት ድርሻው የጎላ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው የአመራሩን አቅም በከፍተኛ ደረጃ የሚገነባ፣ ፓርቲንና መንግስትን የሚያጠናክር ከመሆኑም ባለፈ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግም አንስተዋል፡፡