Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ ነው – አምባሳደር ምስጋኑ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል የጋራ ልማትን ለማረጋገጥና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በሚኖረው ፋይዳ ላይ ከተለያዩ የሲቪል ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ ምክክር እያካሄደ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ÷ የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የብሪክስ አባል መሆን ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለአማራጭ የልማት ፋይናንስ ምንጭን ለማስፋትና አጋርነትን ለማጎልበት የሚረዳ መሆኑን አንስተዋል።

ብሪክስ የሁሉም አመለካከት ማዕከልና በዓለም ትልቅ ምጣኔ ሃብታዊ ጉልበት ያለው ስብስብ እንደሆነም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ድምጿን ለማሰማት ተጨማሪ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ትልቅ የዲፕሎሚሲ ስኬት እንደሆነ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ከየትኛውም ርዕዮተዓለም ጎራ ለመወገን ሳይሆን ከሁሉም የዓለም ሀገራት ጋር የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እንደሆነ አምባሳደር ምስጋኑ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የገፅታ ግንባታ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ዕውቅና እንዲያገኝ በማድረግ በኩል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው÷ የመድረኩ ዋነኛ ዓላማም በብሪክስ ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማስቻል ነው ብለዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው÷ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የውጭ ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ለሀገር አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በብሪክስ አባልነት ጉዳይ ግንዛቤ መፈጠሩም ማህበራቱ የበኩላቸውን ሚና በላቀ መልኩ እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.