ግላኮማ – ሁለተኛው የዓይነ ስውርነት መንስዔ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ግላኮማ የዓይን ሕመም በዓይን ነርቭ ላይ ችግር የሚያስከትል ሲሆን፥ በዓይን ውስጥ የሚገኘው ግፊት በመጨመሩ ምክንያት የሚከሰት ነው።
የዚህ ግፊት መጨመር በዓይን የሚታዩ ምስሎች ወደ አንጎል የሚወስደውን የዓይን ነርቭ የሚጎዳ ሲሆን፥ ይህም በቀጣይነት ቋሚ ለሆነ የዓይን ብርሃን እጦት ይዳርጋል።
በዕድሜ መጨመር ምክንያት ከሚከሰተው የዓይነ ስውርነት በመቀጠል ግላኮማ በዓለም ላይ ሁለተኛው የዓይነ ስውርነት መንስዔ እንደሆነ ይነሳል፡፡
ግላኮማ በሚጀምርበት ጊዜ የሚያሳየው ቀዳሚ ምልክት ወይንም የሕመም ስሜት ስለሌለ ማንኛውም ሰው መደበኛ የሆነ የዓይን ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
ይህም ዓይን ለከፋ ጉዳት ከመጋለጡ በፊት ሕክምና እንዲደረግለት የሚረዳ ሲሆን፥ ከ40 ዓመት እድሜ በላይ ያሉ ሰዎች በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ሃኪም በመሄድ ምርመራ ማድረግ አለባቸው።
የዓይን ውስጥ ግፊት ለምን ይጨምራል?
ግላኮማ የሚከሰተው በዓይን ውስጥ የሚገኘው ግፊት ሲጨምር ሲሆን ፥ ይህ ደግሞ በዘር፣ በኢንፌክሽን፣ በዓይን በቀዶ ጥገና ምክንያት በፊተኛው የዓይን ውስጥ የሚገኘው ፈሳሽ በጤናማ ሁኔታ መንሸራሸር ሲያዳግተው ነው።
በግላኮማ የሚጠቁ ከአርባ አመት እድሜ በላይ የሆኑ፣ በግላኮማ የተጠቃ ቤተሰብ ያላቸው፣ የስኳር ህመምተኞችና የዓይን ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ናቸው፡፡
የግላኮማ ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?
በአብዛኛው ግላኮማ በቅድሚያ የሕመም ምልክት ላያሳይ ቢችልም ከጊዜ በኋላ ግን የመጀመሪያ ምልክት የሚሆነው በጥግ በኩል የሚጀምር የዓይን ብርሃን ችግር ነው።
ምልክቶቹ
• ድንገተኛ የሆነ የአይን ህመም
• ከፍተኛ የራስ ምታት
• የዓይን ብዥታ
• ጥርት ያለ እይታ አለመኖር
• የዓይን መቅላት
• የዓይን ብርሃን ማጣት
• የዓይን እይታ ጥበት ናቸው፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች ሲያጋጥምዎ በአፋጣኝ ወደ አይን ሀኪም መሄድ ይጠበቅብዎታል።
ግላኮማን መከላከል ይቻላል?
ግላኮማ እንዳይከሰት መከላከል የማይቻል ነው ቢባልም በቶሎ የሕመሙ መኖር ከታወቀ ለመቆጣጠርና እንዳይባባስ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
በግላኮማ ምክንያት የተከሰተ የዓይን ብርሃን ጉዳት ተመልሶ ሊስተካከል የማይችል ቢሆንም የነበረው ጉዳት እየተባባሰ እንዳይሄድ ግን የዓይን ግፊት መጠኑን መቀነስ ይቻላል።
ሕክምናቸውን በሚገባ የሚከታተሉ ታካሚዎችም የዓይን ብርሃናቸውን ማዳን እንደሚችሉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።