Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ጣሊያን በአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሞች ትግበራ ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ በዱባይ ተፈራርመዋል፡፡

ከ28ኛው የተመድ አየር ንብረት ጉባኤ ጎን ለጎን በተከናወነው የፊርማ ሥነ ስርዓት ላይ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ጋረደው (ዶ/ር) እና በአካባቢና የኢነርጂ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ አየር ንብረት ኃላዋ ሮበርታ ሮንዚቲ ተፈራርመዋል፡፡

ሥምምነቱ በተለይም በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ለሚከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሞች እንዲሁም የዘላቂ ልማት ስራዎች ላይ መተባበር ላይ ትኩረቱን ያደረገ መሆኑን በዱባይ እና በሰሜን ኢሚሬቶች ከኢትዮጵያ ቆንስላ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ እና በመሳሰሉት ተነሳሽነቶች በአካባቢ ጥበቃ ግንባር ቀደም ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያና በዘላቂ ልማት እና በሃይል ደህንነት መስክ ሰፊ እውቀት ካላት ከጣሊያን ጋር የትብብር መንገዶችን የሚከፍት ነው ተብሏል፡፡

ትብብሩ የብዝኃ ህይወት ጥበቃ፣ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች፣ የቆሻሻ አወጋገድ እና የአየር ንብረት ለውጥ መላመድን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎችን እንደሚያጠቃልል ታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.