ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ባለፈው ሣምንት ያደረጉት ጉብኝትና የጉባዔ ተሳትፎ አመርቂ ውጤት የተገኘበት ነው – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሣምንት ያደረጉት ጉብኝት እና የጉባዔ ተሳትፎ ስኬታማ እና አመርቂ ውጤት የተገኘበት ነው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሣምንት በሦስት ሀገራት ያደረጉትን ጉብኝት የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት አመታዊ ጉባኤ ላይ መገኘት፤ በተመድ የአየር ንብረት ለውጥ የመሪዎች ጉባኤ ላይ መሳተፍ እና ከጉባዔው ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ውይይት ማድረግ እና በቼክ ሪፐብሊክ ይፋዊ መንግስታዊ ጉብኝት ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በ20ኛው የተባበሩት መንግሥታት የኢንደስትሪ ድርጅት ጉባኤ ላይ በክብር እንግዳነት መገኘታቸውን ጠቅሰው፥ በጉባዔው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያደረጉ ሀገራት ተሞክሮዋች መቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከእነዚህ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አንስተው፥ ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ሀገሪቱ ባለፉት አምስት አመታት ባደረገችው የኢኮኖሚ ማሻሻዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል ብለዋል፡፡
በመድረኩም ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያደረገችውን በጎ ልምዶችን አጋርታ አድናቆት እንደተቸራትም ተናግረዋል፡፡
ሆኖም አሁንም ተግዳሮቶች መኖራቸውን ተናግረው እነዚህን ለመቅረፍ የበለፀጉ ሀገራት በፋይናንስ እና በእውቀት ሽግግር ቃል የገቡትን ድጋፍ ለአፍሪካም ሆነ ለኢትዮጵያም ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይ አመት በአዲስ አበባ ሊደረግ የታሰበው ተመሳሳይ ጉባኤ ኢትዮጵያ በተሟላ ሁኔታ ለማስተናገድ ዝግጁ እንደሆነችና ሁሉም ሀገራት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
በሌላ በኩል የበርካታ ሀገራት መሪዎች በተሳተፉበት በኮፕ 28 ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዋናነት ድርጊት ይቅደም የሚለው ላይ ትኩረት አድርገው መናገራቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ተግባር ገብታ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን፣ በአከባቢ ጥበቃ፣ በምግብ ዋስትና ፣ በሌማት ትሩፋት በተለይም በስንዴ ምርት ከግዢ ወደ ላኪነት የተሻጋገረችበትን እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ እየተሰሩ ያሉ ጅምር ስራዎችን እንደ ማሳያ አቅርበዋል፡፡
ይህን መሰል ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ትኩረት ያደረገን ስራ የበለፀጉ ሀገራት መደገፍ እንደሚገባቸውም ዐቢይ(ዶ/ር) ተናግረዋል ነው ያሉት፡፡
በጉባዔው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መካነ ርዕይ /ፓቪሊዮን/ በተለይ የኢትዮጵያ ቡና የበርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ መሳቡን ተናግረዋል፡፡
ከጉባዔው ጎን ለጎን ጠ/ሚ ዐቢይ(ዶ/ር) ከበርካታ ሀገር መሪዎችና ከልማት ተጠሪዎች ጋር ለኢትዮጵያ አጋርነትን የማስፋት ፣የፋይናንስ እና ኢንቨስትመትን ድጋፍ የሚጠናከርበት ዙሪያ ያተኮረ ውይይት መደረጉንም አውስተው በዚህም አዎንታዊ ምላሽ መገኘቱን እና ስኬታ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቼክ ሪፐብሊክ ቆይታቸው ከመሪዎች እና ከቼክ ባለሃብቶች ጋር መምከራቸውን እና የግብርና መካናይዜሽንን የሚደግፉ የኢንዱስትሪ መስኮችንና ሌሎችንም መጎብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ እና በግብርና፣በማኑፋክቸሪንግ፣በማዕድን በቱሪዝም እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ በጋራ ለመስራት መስማማት ላይ መደረሱንም ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ ሁለቱም ስብሰባዎች የኢትዮጵያ ስኬት ጎልቶ የታየበት፣ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ግብና ስኬት ከሰሩ አመርቂ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ይህም ውጤታቸው በአለም አቀፍ የኢትዮጵያን ገፅታ እንደሚገነባ የታየበት ነው ብለዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው