Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከነገ ጀምሮ ለተባባሪ አካላት ስልጠና ሊሰጥ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለተባባሪ አካላት ከነገ ጀምሮ ስልጠና መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ።

ከህዳር 26 እስከ 28 ቀን 2016 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚሰጠው ስልጠና በሀገራዊ ምክክሩ ተሳታፊ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አካላትን የሚለዩ ተባባሪ አካላት እንደሚሳተፉ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገልፀዋል።

ስልጠናው በክልሉ ለሚደረገው የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታን ለማከናወን እንደሚረዳም ተናግረዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች ወደ 700 የሚጠጉ ተባባሪ አካላት መሆናቸውን እና ከሁሉም የክልሉ ዞኖች ከሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሰልጣኞችም ከሰልጠናው በኋላ ወደየአካባቢያቸው ሲመለሱ ተሳታፊዎችን በገለልተኝነትና አካታችነት በመለየቱ ሂደት ላይ ለኮሚሽኑ እገዛ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ሲሉ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ገልፀዋል፡፡

ስልጠናውን የሚወስዱ ተባባሪ አካላትን የሚወክሉ ከኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ ከክልሉ ሲቪክ ማህበራት ምክር ቤት፣ በክልሉ ከሚገኘው ኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ከክልሉ መምህራን ማህበር፣ ከክልሉ የዕድሮች ማህበራት ጥምረት፣ ከወረዳ አስተዳደር (ከተማ አስተዳደር) ተወካይ እና ከየወረዳዎች እና ከከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ዳኞች መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ ናቸው፡፡

በመለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.