Fana: At a Speed of Life!

የቡና ግንድ አድርቅ በሽታን መከላከል የሚያስችል መድኃኒት በምርምር ተገኘ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቡና ግንድ አድርቅ በሽታን መከላከል የሚያስችል መድኃኒት በምርምር ማግኘቱን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው የቡና ግንድ አድርቅ በሽታን በምስራቅ አፍሪካ በምርታማነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ያለመ አውደ-ጥናት አካሂዷል፡፡

የቡና ግንድ አድርቅ በሽታ መድኃኒት የሌለው ሲሆን በከፍተኛ ሁኔታ የቡና ምርታማነት ላይ ጉዳት እያደረሰ የሚገኝ ነው፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከመካከለኛው አፍሪካ አገራት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አፍሪካ በስፋት የሚከሰት፤ በፈንገስ አማካኝነት የሚተላለፍ በሽታ መሆኑ በአውደ-ጥናቱ ላይ ተገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ÷ በምስራቅ አፍሪካ በቡና ምርታማነት ላይ ጉዳት እያደረሱ ከሚገኙት በሽታዎች መካከል የቡና ግንድ አድርቅ በሽታን ለመከላከል የተሰራው የምርምር ሥራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ተስፋዬ አለሙ(ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ባለፉት 18 ዓመታት ባካሄዱት ምርምር የቡና ግንድ አድርቅ በሽታን መከላከል የሚያስችል ”ትራያስፐር ባዮፈንጊሳይድ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሥነ-ህይወታዊ መድኃኒት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

መድኃኒቱ 70 በመቶ በፈንገስ የሚተላለፍ የቡና ግንድ አድርቅ በሽታን መከላከል የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

እንዲሁም በቡና ግንድ አድርቅ የሚደርስን የምርት ጉዳት ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በምርምር የተገኘው መድኃኒትም በምስራቅ አፍሪካ በስፋት ጉዳት እያደረሰ ያለው የቡና አድርቅ በሽታን ለመከላከል ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መድኃኒቱን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በኬንያና በዩጋንዳ ተደራሽ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

1 ኪሎ ግራም የቡና ግንድ አድርቅ መከላከያ መድኃኒት ”ትራያስፐር ባዮፈንጊሳይድ” ለ2 ሺህ የቡና እግር የሚያገለግል ሲሆን፤ በውህድ መልክ አፈር ውስጥ በማድረግ ወይም በቅርንጫፍ ላይ በመርጨት መጠቀም የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መድኃኒቱ በአካባቢ ላይም ሆነ በቡና ጥራት ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ የማይፈጥር መሆኑን በተለያዩ አገራት ተመራማሪዎች ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.