የሸዋል ኢድ በዓል የቱሪስት መዳረሻነቱን ለማሳደግ በትኩረት እንሰራለን- የሐረሪ ክልል የባህል ቡድን አባላት
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሸዋል ኢድ በዓል የቱሪስት መዳረሻነቱን ለማሳደግ በትኩረት እንሰራለን ሲሉ የ18ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የተሳተፉ የሐረሪ ክልል የባህል ቡድን አባላት ገለጹ።
ሸዋል ኢድ የሐረሪ ህዝብ ባህላዊ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የትምህርት ተቋም (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ እንዳስደሰታቸው አባላቱ ተናግረዋል።
በቀጣይ የበዓሉን የቱሪስት መዳረሻነት ለማስፋትም በትኩረት እንደሚሰሩ ነው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የገለጹት።
በተለይም በበዓሉ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች እንዲሳተፍና ባህላዊ እሴቱን እንዲገነዘቡ በመሠል ሁነቶች በዓሉን የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል ብለዋል።
ለዚህም ከክልል እና ፌዴራል የሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ጠቅሠዋል።
የሸዋል ኢድ በዓልን በብሔረሰቦችና እምነቶች መቻቻል መካከል ያለውን አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እንዲከበርና ሌሎች ሕዝቦችን ለማሳተፍ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችና ትውፊቶች በህዝቦች መካከል የእርስ በእርስ አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ የኢኮኖሚ ፋይዳ እንዲኖራቸው እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።