የትግራይ ልማት ማህበር ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች በማፍራት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እያገዘ ነው-አቶ ጌታቸው ረዳ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ልማት ማህበር በክልሉ ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች በማፍራት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን እያገዘ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በትግራይ ልማት ማህበር የተገነባውና 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሚያከብረው የቃላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተዘጋጀ ሥነ ስርዓት ላይ ተገኝተዋል፡፡
በዚህ ወቅት እንደገለፁት ልማት ማህበሩ ያስገነባው የቃላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በክልሉ ውስጥ ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።
ባለፉት 25 ዓመታት በዚሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በርካታ አቅምና ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች መገኘታቸውን ጠቁመው፥ “የልማት ማህበሩ በሀገራችን በተለያዩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስራዎች በመሰማራት መሰረታዊ እድገት እንዲመዘገብ ድርሻው የላቀ ነው” ብለዋል።
ልማት ማህበሩ ዲጂታል ትምህርትን በማስፋፋት የመማር ማስተማር ሂደቱን የዘመነ ለማድረግ የያዘው ራዕይ እውን እንዲሆን የክልሉ ህዝብ ከጎኑ በመሰለፍ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የልማት ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ የማነ ታደሰ (ኢ/ር) በበኩላቸው፥ በ12 ከተሞች ቃላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት ተጀምሮ ግንባታቸው የተቋረጡትን ዳግም ግንባታቸውን ለማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡