Fana: At a Speed of Life!

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐረሪ ክልል 392 ተወካዮች መለየቱን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐረሪ ክልል 392 ተወካዮች መለየቱን አስታወቀ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሐረሪ ክልል በተካሄደው የተሳታፊዎች ልየታና በህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ዙሪያ የምክክር መድረክ አካሒዷል፡፡

በመድረኩ ኮሚሽኑ በክልሉ ያከናወናቸው ተግባራት ላይ ገለጻ የተደረገ ሲሆን÷ በዚህም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ዙሪያ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ስለመሆናቸው ተገልጿል።

ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሐረሪ ክልል 3 ሺህ 720 የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈው 392 ተወካዮች መለየታቸውም በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡

ተወካዮች ሲመረጡ ሐረር ከተማ ብሔሮች ብሔረሰቦች በአብሮነት የሚኖሩባት እንደመሆኗ የሁሉምን ማህበረሰብ ስብጥር ያካተተ እንዲሁም ፆታንና እድሜንም መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ ተገልጿል።

የቋሚ ኮሚቴው አባልና አስተባባሪ ወ/ሮ አቡኔ አለም በዚሁ ወቅት÷ በሐረሪ ክልል ያለው የመቻቻል እና የአብሮነት እሴት ተምሳሌት ነው ብለዋል።

የምክክር መድረኩ በተከታታይ ቀናት ከመንግስት አካላት እና ከህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚቀጥል መሆኑን የክልሉ መገናኛ ብዙሐን ዘግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ግንኙነትን እንዲሁም ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ለመጠገንና ሀገራዊ አለመግባባቶችን ለመፍታትም ኮሚሽኑ እንደተቋቋመ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.