ከጥራጥሬና ቅባት እህሎች 159 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አራት ወራት ከ184 ሺህ ቶን በላይ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ለውጭ ገበያ በማቅረብ 159 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው÷ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ወጪ ንግድ ለማሳደግ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይቷል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አራት ወራት ከጥራጥሬ ሰብሎች ከ119 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዲሁም ከቅባት እህሎች ከ39 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉ ተገልጿል፡፡
የሰሊጥ ምርት የዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋ መቀዛቀዝና በጸጥታ ምክንያት በቂ ምርት ለውጪ ገበያ መቅረብ እንዳልቻለ ተነግሯል።
የኑግና የጉሎ ፍሬ ምርት ክምችት በበቂ ሁኔታ አለመኖር በወጪ ንግድ አፈፃፀሙ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ ተመላክቷል፡፡
በቀጣይ የዘርፉን ወጪ ንግድ ይበልጥ ለማሻሻል ምርት በወቅቱ ተመዝኖ ለውጭ እንዲላክ ለማድረግና የኮንትራት ምዝገባና የመላኪያ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በመሆኑም ላኪዎች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ለተቀላጠፈ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።