በሀገራዊ ምክክሩ አካል ጉዳተኞ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ተባለ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን አካል ጉዳተኞች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ÷ በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በሚያጋጥሙ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ ዜጎች ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም በማያግባቡ አጀንዳዎች ላይ ቁጭ ብሎ ተወያይቶ ዘላቂ መፍትሄ ስላልተበጀ ነው ብለዋል።
አንድ ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ÷ ለዚህም ለግጭትና ሰላም መደፍረስ ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን በውይይት እልባት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት የተቋቋመው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለምክክሩ ውጤታማነት የሁሉም ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑም አካል ጉዳተኞች በምክክሩ ንቁ ተሳተፊ በመሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የሚያስችል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተለያዩ አደረጃጀቶች የሚያከናውናቸው ሥራዎችም አካል ጉዳተኞችን ያካተተ እንዲሆን የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ምክክሩን ስኬታማ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አካል ጉዳተኞች የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል ትኩረት ይደረጋል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡