ላዳ ታክሲዎችን በአዲስ ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ለደገፉ አካላት ምስጋና ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ታኀሣስ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እድሜ ጠገብ የላዳ ታክሲዎችን በአዲስ ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ለደገፉ አካላት ምስጋና የማቅረብ መርሃ ግብር በወዳጅነት ፓርክ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የገንዘብ ሚኒስቴርን ጨምሮ አሮጌ የሆኑትን የላዳ ታክሲዎች በአዲስ ለመተካት የተደረገውን ጥረት ለደገፉ አካላት ምስጋና ቀርቧል።
በተለይም ላዳ ታክሲዎችን በአዲስ ለመተካት በተደረገው ጥረት ከቀረጥ ነጻ ፍቃድ መሰጠቱ ሂደቱን እንዳቀላጠፈው ተገልጿል።
አዲስ አበባ ከተማን በሚመጥኑ አዳዲስ ዘመናዊ ታክሲዎች ለመስራት የብድር አማራጭ ሲፈልጉ የነበሩ የላዳ ባለንብረቶች ማህበራት የብድር አማራጭ ኦክሎክ ሞተርስ ከአሚጎስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃ/የተ/የህብረት ስራ ማህበር ጋር እንዲሰሩ ብድር ማመቻቸቱ ተነግሯል።
በዚህም የብድር አማራጭ ችግሩ መፈታቱን የማህበራቱ ጥምር ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዘውዱ በቀለ ተናግረዋል።
ዘመናዊ መኪናዎችን በሀገር ውስጥ የሚገጣጥመው ኦክሎክ ሞተርስ ዘመናዊ መኪኖቹን ለማህበራቱ አባላት በማቅረብ ላይ ይገኛል።
በላዳ ታክሲ ባለቤቶች እና የትራንስፖርት ዘርፉን በአዲስ መልክ ሊቀላቀሉ በሚፈልጉ ሰዎች የተመሰረቱት 60 ማህበራት በአጠቃላይ 3 ሺህ ገደማ አባላት አላቸው።
በህይወት አበበ