የገና በዓልን በላሊበላ ከተማ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገና በዓልን በላሊበላ ከተማ በድምቀት እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የከተማዋ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ወንድምነው ወዳጄ እንደገለፁት÷ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች መዳረሻ በሆነችው ላሊበላ ላለፉት አምስት አመታት በኮሮና ወረርሽኝና በጦርነት ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴዋ ተዳክሞ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ ላሊበላን ልክ እንደበፊቱ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በተለይም ታህሳስ 29 በከተማዋ በድምቀት የሚከበረውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ አንድ አብይ እና ሥድሥት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው የቅድመ ዝግጅት ሥራቸውን መጀመራቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልፀዋል፡፡
ለበዓሉ ዝግጅት ወጣቶች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ባለሐብቶች እና የመንግሥት አካላት በቅንጅት እየሠሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያን እንደወትሮው ሁሉ ገናን በላሊበላ እንዲያከብሩም ተቀዳሚ ከንቲባው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በሰሎሞን ይታየው