በክልሉ በመኸር ወቅት የተገኘውን የስንዴ ልማት ውጤት በበጋ ለመድገም እየተሰራ ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመኸር ወቅት በስንዴ ሰብል ልማት የተገኘውን አበረታች ውጤት በበጋ ለመድገም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡
በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ በአሶሳ ዞን አቡራሞ ወረዳ የበጋ ስንዴ የስራ እንቅስቃሴን እና የፓፓያ ክላስተርን ጎብኝተዋል።
አቶ አሻዳሊ በወቅቱ እንደገለጹት÷ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው።
በክልሉ በ2015/16 የመኸር ወቅት የተገኘውን አበረታች የስንዴ ውጤት በበጋ መስኖ ስንዴም ለመድገም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በክልሉ ስንዴን በስፋት በማልማት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ባለፉት ጊዜያት የተገኙት ውጤቶች ማሣያ ናቸው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
መንግስት አርሶ አደሩን ከዝናብ ጠባቂነት ወጥቶ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።