Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ሥምምነት የኢትዮጵያን የንግድ ትስስር ያጠናክራል – አቶ ገብረመስቀል ጫላ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት ኢትዮጵያን በዓለም ገበያ ውስጥ ያላትን የንግድ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ከሶማሊላንድ ጋር መፈሟን ተከትሎ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ÷ ለሚኒስቴሩ ሠራተኞችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው የባህር በር አለመኖር በሀገሪቱ የገቢና የወጪ ንግድን እንዲሁም ሀገሪቱ በዓለምና በቀጣናዊ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ የባህር በር ለማግኘት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት ይህን ችግር የሚቀርፍና የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ንግድ ተሳትፎ የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ይህም ሀገራዊ የንግድ መጠንና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም አውስተዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው÷ ሥምምነቱ የወጪና የገቢ ንግድን በማቀላጠፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሥምምነቱ ወደ ትግበራ ሲገባ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ያሉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍሰሃ ይታገሱ ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.