Fana: At a Speed of Life!

በሙስና ወንጀል የተጠረጠረ የፍርድ ቤት ዳኛ በቁጥጥር ስር ውሎ ፍርድ ቤት ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሙስና የወንጀል ድርጊት በመፈጸም ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ዳኛ ፍርድ ቤት ቀረበ።

ተጠርጣሪው የአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆነው ተስፋዬ ደረጄ በወንጀል የተከሰሰ ግለሰብን ነጻ አደርግሃለው በማለት በሙስና ገንዘብ ተቀብሏል ተብሎ ተጠርጥሯል።

ተጠርጣሪው አንድን ግለሰብ ከተመሰረተበት የወንጀል ክስ ነጻ አስወጣለው በማለት የግለሰቡን መዝገብ የሚመለከቱ ሁለት ዳኞች አብረውት እንደተማሩና እንደሚያውቃቸው እንዲሁም አንደኛውን ዳኛ ደግሞ የስራ ባልደረባዬ ያውቃቸዋል ብሎ በመግለጽ በማግባባት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በመጠየቅና 400 ሺህ ብር ሙስና ተቀብሏል በሚል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሏል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር በማዋል፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ተጠርጣሪውን ዛሬ ፍርድ ቤት አቅርቧል።

ሆኖም የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ባሉበት ተደራራቢ የመዝገቦች ምክንያት በይደር ለመመልከት ለነገ ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.