Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ባለው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው።

“መተማመንን ዳግም መገንባት” በሚል ጭብጥ ለ54ኛጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የዘንድሮው ጉባኤ፥ ቁልፍ በሆኑ ዓለም አቀፍ የልማት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ አየር ንብረት ለውጥና ወቅታዊ የደህንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

አቶ ደመቀ በጉባኤው ተሳትፏቸው ጎን ለጎን ከሀገራት መሪዎች እና ከተቋማት ሃላፊዎች ጋርም ውይይት አድርገዋል።

ከታንዛኒያ ምክትል ፕሬዝዳንት ፊሊፕ ምፓንጎ ጋር በነበራቸው ውይይትም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ያብራረሩ ሲሆን ፕሮጀክቱ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ገልፀውላቸዋል።

የታንዛኒያ ምክትል ፕሬዝደንት ፊሊፕ ምፓንጎ በበኩላቸው፥ በአባይ ውሃ ሃብት ላይ ፍትሃዊ አጠቃቀም በተፋሰሱ ሀገሮች መካከል እንዲሰፍን ሀገራቸው የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶች በውይይት እንዲቋጩ ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ሊቀጥል እንደሚገባም ገልጸዋል።

የሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባን በቅርቡ ለማካሄድ ተስማምተዋል።

አቶ ደመቀ ከዓለም አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዳረን ታንግ ጋር በነበራቸው ውይይትም ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላት ትብብር ሊጠናከር በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗንም ተናግረው፤ ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ አቶ ደመቀ ያቀረቡላቸው ጥሪም ተቀብለዋል።

ዋና ዳይሬክተር ዳረን ታንግ የአለም አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ድርጅት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡ (FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.