የሲዳማ ክልል የከተራና ጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ቅድመ ዝግጅት አድርጌያለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል የከተራና ጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበር የጸጥታ ሃይሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ሽመልስ ቶማስ እንደገለጹት ÷ ኮሚሽኑ ከፌደራል፣ ከክልልና ከተማ ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በአደባባይ የሚከበረው በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል።
ኮሚሽኑ ከሐዋሳና ከክልሉ ነዋሪዎች፣ የእምነት ተቋማትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በበዓሉ አከባበርና በሰላም ዙሪያ መወያየቱንም ነው የገለጹት።
ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን ህዝቡ በተለመደ ጨዋነት እንዲያስተናግድ ጠይቀው ÷ ሆቴሎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም ያለምንም ጭማሪ እንዲያስተናግዱ ምክክር ተደርጓል ነው ያሉት።
በዓሉን ምክንያት በማድረግም የተቋቋሙ ጊዜያዊ ችሎቶች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን ÷ ለተሽርካሪም ዝግ የሚሆኑ መንገዶች እንደሚኖሩ ተጠቅሷል፡፡
በሐዋሳና በክልሉ በዓሉ በድምቀት በሚከበርባቸው አካባቢዎች የትራፊክ መጨናነቅ እንዳያጋጥም የሚመለከታቸውን አካላት ያሳተፈ ውይይትና ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል መባሉን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በቅንጅት የሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በበኩላቸው ÷ የበዓሉ በሰላም መከበር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የሚጠበቅብንን እንወጣለን ብለዋል።