Fana: At a Speed of Life!

የአንድሬ ስቴኒን ዓለም አቀፍ ፕሬስ ፎቶ ውድድር ሥራዎች ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፍ ወጣት ፎቶ አንሺዎችን ሥራዎች የሚያሳትፈው የአንድሬ ስቴኒን ዓለም አቀፍ ፕሬስ ፎቶ ውድድር ሥራዎች ለሕዝብ የሚታዩበት ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ።

የአንድሬ ስቴኒን ፕሬስ ፎቶ ውድድር ‘ራሽያ ሲጎኒያ’ ወይም የ’ራሺያ ቱደይ’ የሚሰኘው የሩሲያ የሚዲያ ተቋም አዘጋጅነት በመላው ዓለም የሚገኙ ወጣት ፎቶ አንሺዎ የሚሳተፉበት ፕሮጀክት ነው።

ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 33 የሆኑ ወጣቶች የሚሳተፉበት ውድድር ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ የተወዳዳሪዎችን ምዝገባ በይፋ ጀምሯል።

የሩሲያ ሲጎኒያ የዓለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ኃላፊ ክሪስቲና ሊያክ እንዳሉት÷ውድድሩ በተለያዩ አጋጣሚዎችና በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች የተነሱ ፎቶግራፍ ሥራዎችን በበይነ መረብ ተቀብሎ በማወዳደር ወጣት ባለተሰጥኦ የዓለማችን ወጣት ፎቶ አንሺዎችን የሚያበረታታ ነው።

በውድድሮች በአሸናፊነት የተመረጡ ከ50 በላይ ፎቶግራፎች በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ለህዝብ ዕይታ ይቀርባሉም ተብሏል።

የአንድሬ ስቴኒን ፕሬስ ፎቶ ግራፍ ዐውደ ርዕይ በሩሲያ ባህልና ሳይንስ ማዕከል ከቀናት በፊት በይፋ የተከፈተ ሲሆን÷ ከቅዳሜ ጥር 18 እስከ የካቲት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚጎበኝ ተገልጿል፡፡

ከአዲስ አበባ በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ፣ በአርጀንቲና እንዲሁም በሰርቢያ ዋና ከተሞች የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕዩ ተከፍቷል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢያቭገኒ ተርኪን በፎቶ ዐውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ÷ዐውድ ርዕዩ የዘመኑን ፎቶግራፍ ጥበብ ለመመልከት ብሎም ኢትዮጵያውያን ፎቶ አንሺዎች በቀጣይ ውድድር ተሳታፊ እንዲሆኑ ተነሳሽነት ይፈጥራል።

በዘንድሮው የአንድሬ ስቴኒን ፎቶግራፍ ውድድር አምስት የውድድር ፈርጆች ያሉት ሲሆን÷ ለአሸናፊዎች ትልቁ ሽልማት 700 ሺህ የሩሲያ ሩብልን ጨምሮ እንደየደረጃቸው ከ75 እስከ 125 ሺህ ሩብል ሽልማት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።

በዘንድሮው የፕሬስ ፎቶ ውድድር መሳተፍ ለሚሹ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም ከታች ያለውን ሊንክ በመጠቀም መሳተፍ እንደሚችሉ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

https://stenincontest.com/register/#register

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.