ከ9 ሚሊየን ብር በላይ መንግስትን አሳጥተዋል የተባሉ ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ9 ሚሊየን ብር በላይ ዓመታዊ ግብር ክፍያ መንግስትን አሳጥተዋል የተባሉ ግለሰቦች በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ እስከ 13 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾቹ 1ኛ በግል የስራ ተቋራጭ የሆኑት አብይ አማረ ዋሴ እና የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ የሒሳብ ባለሙያ የነበሩት ተረፈ ቦጃ ናቸው።
የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ሁለት የወንጀል ክሶችን በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ባጠቃላይ በ3 ተከሳሾች ላይ ክስ መመስረቱን መዘገባችን ይታወሳል።
ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 33 እንዲሁም ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ የተመላከተውን ድንጋጌ እና የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 203/2009 አንቀጽ 118 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚል ነበር።
በዚህም በአንደኛ ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን በሁለተኛው ክስ ላይ ደግሞ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ ነው የቀረበው።
በክሱ እንደተመላከተው 1ኛ ተከሳሽ የታክስ አስተዳደር አዋጁን በመተላለፍ ዓመታዊ የግብር ገቢ መክፈል ሲገባቸው የከፈሉ ለማስመሰል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠመንጃ ያዥ ቅርንጫፍ የተሰጠ የሚመስል ሀሰተኛ የኦሮሚያ ገቢዎች ሒሳብ ያልሆነ የባንክ ስሊፕ ማቅረባቸው በክስ መዝገቡ ላይ ተመላክቷል፡፡
2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ደግሞ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ያቀረቡትን ሐሰተኛ የባንክ ስሊፕ ሕጋዊነት ማረጋገጥ ሲገባቸው÷ ሳያረጋግጡ ሀሰተኛ ስሊፑን እና ሌሎች ሰነዶችን ትክክለኛነት ሳያረጋግጡ በመቀበል የገቢ ግብር ከፍለዋል በማለት የገቢ ደረሰኝ መስጠታቸው ተጠቅሷል፡፡
ከዚህም በኋላ ደግሞ ስራ ተቋራጩ ዓመታዊ ግብር ከነቅጣቱ እንደከፈሉ በማስመሰል ዓመታዊ ግብር ባለመክፈላቸው ምክንያት የተጣለባቸው የንብረት እግድ እንዲነሳላቸው በ3ኛ ተከሳሽ በኩል ለህግ ክፍል መጻፉም በክሱ ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ መንግስትን 9 ሚሊየን 292 ሺህ 127 ብር ከ83 ሳንቲም ገቢ አሳጥተዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸዋል።
ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ዝርዝር ደርሷቸውና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸው ሰጥተዋል።
ይህን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ከ3 በላይ የሰው ምስክሮችን እና ሌሎች ገላጭና አስረጂ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።
የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን የመረመረው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን የመከላከያ ማስረጃ ያቀረቡ ሲሆን 1ና 2ኛ ተከሳሾች ባቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው አላስተባበሉም በማለት በፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
3ኛ ተከሳሽ የነበሩት የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ የግብር ክትትል ቡድን መሪ መንግስቱ ሙሉነህን በሚመለከት የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን አስተባብለዋል በሚል ከቀረበባቸው ክስ ነጻ ተብለዋል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ እንዲሁም ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ አስተያየትን መርምሮ ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ የቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል።
በዚህም የተከሳሾችን የቅጣት አስተያየት በመያዝ 1ኛ ተከሳሽን ጥፋተኛ በተባሉበት ድንጋጌ በዕርከን 32 መሰረት በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በ85 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኗል።
2ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በአንድ አመት እስራትና በ2 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ የወሰነ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ በኩል ይግባኝ እንደሚጠይቅ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቋል።
በታሪክ አዱኛ