Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 6 ወራት የውስጥና የውጭ ጫናዎችን ተቋቁመን ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግበናል – አቶ አሕመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ስድስት ወራት የውስጥና የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም በዋና ዋና የዕድገት ምንጮች የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ ገለፁ።

የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ በዐበይት ሀገራዊ ጉዳዮች እና በልዩ ልዩ የፓርቲ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቅቋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው ባለፉት ስድስት ወራት አጠቃላይ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምን መልክ እንደነበረው መምከሩ ተገልጿል።

የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ እንዳሉት÷ ባለፉት አምስት ዓመታት መንግስት በተከተለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አበረታች እድገት እየተመዘገበ ይገኛል።

በዚህም በተከታታይ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት ከብዙ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አፈጻጸም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የግሉን ሴክተር በንቃት በሚያሳትፍና በሚያበረታታ መልኩ የተነደፉ ፖሊሲዎች ለውጤታማነቱ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ዘርፈ ብዙ የእድገት ምንጭ ስትራቴጂ መተግበሩም ኢኮኖሚው ጫናዎችን በመቋቋም በተከታታይ እንዲያድግ ማድረጉን ተናግረዋል።

የዕድገት ምንጭ የሆኑ የመንግስት፣ የግል እና የህዝብን አቅም በማስተባበር የተሰሩ ስራዎች ውጤት ማስገኘታቸውንም አስረድተዋል፡፡

በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም እና በሜጋ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ ውጤታማ ስራ መከናወኑንም አመላክተዋል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጫናን በመቋቋም በዋና ዋና የዕድገት ምንጮች የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል ነው ያሉት፡፡

የዋጋ ንረትን ከመቆጣጠር አንፃር ባለፉት ስድስት ወራት መሻሻል መኖሩን ጠቅሰው÷ በዚህ ረገድ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ከልማት አጋሮች ጋር በትኩረት ከመስራት ባሻገር የወጪ ንግድን በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎችም ጥሩ አፈፃፀም እያስመዘገቡ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ካለው ፍላጎት አንፃር የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ በበለጠ ትኩረት መሰራት እንደሚገባ ሚኒስትሩ አመላክተዋል።

በቀጣይ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች መዳረሻ እና አዳዲስ የገበያ አማራጮችን የማስፋት ስራ በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ዕዳ በመክፈል ረገድ ጠንካራ ስራ መሰራቱን ገልጸው አዲስ የንግድ ብድር አለመፈጸሙን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራትም ከዕዳ ጫና ቅነሳና ሽግሽግ አኳያ ስኬታማ ስራ መከናወኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከልማት አጋሮች ጋር ያለው ትብብር እያደገ መምጣቱን ገልጸው ይህም ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዓለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከአውሮፓ ህብረት እና ከሌሎች አካላት ጋር ያለው ትብብር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በተለይ ከዓለም ባንክ ጋር ያለው የልማት ትብብር ወደ ተሟላ መደበኛ ማዕቀፍ የተገባበት መሆኑን ነው የገለጹት።

በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያስመዝገበውን ዕድገት በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ውድነት እንዲሁም የዕዳ ጫና ማቃለል ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ሆነው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የሪፎርም እና የልማት ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

ህዝቡ ለልማት ያለው ከፍተኛ ፍላጎትና ጠንካራ ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.