መመሪያው የአክሲዮን ገዥዎችን መብት ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና አለው – የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈቃድ ለመስጠት የተዘጋጀው መመሪያ የአክሲዮን ገዥዎችን መብት ከማስጠበቅ አንፃር ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ የሕግ አማካሪ አቶ እስጢፋኖስ መልካሙ÷ ፈቃድ ለመስጠት የተዘጋጀው መመሪያ በገበያው ተሳታፊ ለሚሆኑ ተቋማት እና ግለሰቦች የአገልግሎት ፈቃዶችን መስጠት የሚያስችል ሆኖ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ባልተማከለ መንገድ የሚደረገውን የአክሲዮን ግብይት ሕግ፣ ሥርዓትና ቁጥጥር የሚደረግበት ግብይት በማድረግ ሀገርም ሆነ የገበያ ተዋንያን ከዘርፉ የሚያገኙትን ጥቅም የሚያረጋግጥ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የካፒታል ገበያ ወይንም ሰነደ ሙዓለ ንዋይ በገንዘብ ሊተመን የሚችል ባለቤትነትን የሚገልጽ ሰነድ ሲሆን÷ ሊሸጥ፣ ሊለወጥ ወይም በዋስትና ሊሰጥ የሚችል መብት የሚያቋቁም ሰነድ መሆኑን አማካሪው አስረድተዋል፡፡
ዓለም በሥርዓቱ መጠቀም ከጀመረ መቀየቱን ጠቅሰው÷ ኢትዮጵያም በአንድ ወቅት ጀምራ ተቋረጦ ወደነበረው የካፒታል ገበያ ሥርዓት ለመግባት ከጫፍ ደርሳለች ብለዋል።
የካፒታል ገበያ ባለስልጣንን በሕግ ከመቋቋም ተጀምሮ አሁን ላይ ለተለያዩ አገልግሎቶች ፈቃድ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
መመሪያው የአክሲዮን ገዥዎችን መብት ከማስጠበቅ አንፃር ጉልህ ሚና እንዳለው የገለጹት አማካሪው÷ ለዘርፉ ተዋንያን የሥራ ዕድሎችን እና አዳዲስ አሰራሮችን ይዞ ይመጣል ብለዋል።
ለሕግ ማዕቀፉ መዘጋጀትም ትክክለኛውን የሰነዶች ዋጋ እና የአክሲዮን ማህበራት ትክክለኛ ሃብት ማወቅ የሚቻልበት አግባብ አለመኖር እና ሌሎች ምክንያቶችን አንስተዋል፡፡
መመሪያው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ግብይቱን በሕግ ማዕቀፍ የተደገፈ እንዲሆን ከማድረጉ በተጨማሪ ፈቃድ የሌላቸው አገልግሎት ሰጪዎች አገልግሎት መስጠት እንዲያቆም የሚያደርግ መሆኑ ተነግሯል።
በመራኦል ከድር