ብልፅግና ፓርቲ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ እየሰራ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልፅግና ፓርቲ በሀገሪቱ የተፈጠሩ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ እየሰራ ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባልና የኦሮሚያ ክልል ርዕስ መስተዳደር ሺመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡
የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሰቆጣ ከተማ ተገኘተው ከህዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ የዋግኽምራ ብሔረሰብ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ ÷ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በዞኑ ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት በአካባቢው በጎ ተፅዕኖ ማምጣቱን ገልፀዋል፡፡
በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭትቶ በወንድማማቾች መካከል የሚደረጉ በመሆናቸው እና ትርፍ የማይገኝባቸው በመሆኑ ሁሉም ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲመጣና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸው÷ በክልላችን ታስቦ የነበረው የጥፋት እቅድ ተቀልብሷል፣ አንፃራዊ ሰላም ተገኝቷል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባልና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ÷ የገጠሙንን የግጭት አዙሪቶችና ፈተናዎችን በሕብረትና በአንድነት ታግለን ከድህነትና ጉስቁልና መውጣት ይገባናል ብለዋል።
ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ህግና ስርአት መከበር እንዳለበት እና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ትጥቅ በማንገብ ጥያቄን ለማስመለስ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ለማንም የማይጠቅምና ማንም የማያተርፍበት መሆኑን ገልፀዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አለመግባባቶች በንግግር እንዲፈቱ እየሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ሽመልስ÷ ፓርቲው ጽኑ የሰላም ፍላጎት እንዳለው አረጋግጠዋል።
የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባልና የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የዋግኽምራ ሕዝብ ያለውን ፀጋና ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀም በብሔረሰብ አስተዳደሩ የሚነሱ የመልማት ጥያቄዎች በተጨባጭ እንዲፈቱ እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ በሀገሪቱ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች እንዳይቀጥሉ፤ የቀደሙ የልማት አውታሮችም አገልግሎት እንዳይሰጡ ለማድረግ አልመው የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የእኔ ብቻ በሚል አስተሳሰብ በመታጠር ሕዝብና ሀገርን እየረበሸ ያለውን ጽንፈኝነት ሕግና ስርዓትን በማስከበር ከኢትዮጵያ ምድር ማስወገድ ይገባል ማለታቸውን የብልፅግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል፡፡