የዓለም የሚጥል ህመም ሳምንት በተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚከበር ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 01፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም የሚጥል ህመም (ኤፒሌፕሲ) ሳምንት “የሚጥል ህመም ላይ ያለው መገለል እንዲቆም ድምጽ እንሁን!” በሚል መሪ ሀሳብ ከየካቲት 4 እስከ 17 ቀን 2016 በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አስተማሪ ፕሮግራሞች እንደሚከበር ተገልጿል፡፡
ኤፒሌፕሲ የፈጣሪ ቁጣ ወይም በእርግማን ምክንያት የሚከሰት ሳይሆን በድንገተኛና ከቁጥጥር ውጭ በሆነ የአዕምሮ ተግባርን የሚያውክ ክስተት ተከስቶ በአንጎል ነርቭ ውስጥ የኤሌክትሪካዊ ንዝረት ጊዜያዊ መረበሽ ምክንያት የሚከሰት ህመም መሆኑ ተነግሯል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በዓለም 50 ሚሊየን የሚደርስ ህዝብ ከሚጥል ህመም ጋር እንደሚኖር እንደሚገመትና አምስት ሚሊየን ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ በዚህ በሽታ እንደሚያዙ ገልፀዋል።
የሚጥል ህመም መንስኤ በቋሚነት ባይታወቅም አዕምሮ ላይ በሚከሰት መጎዳት፣ በካንሰር ህመም፣ በስትሮክ እንዲሁም በወሊድ ወቅት እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል ተናግረዋል።
በማንኛውም ጾታ እና የእድሜ ክልል ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን የሚጥል ህመምን ከመከላከል እስከ ማዳን የሚደርሱ ስራዎችን ለማገዝ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የህክምና አገልግሎቱን ከሱስ ማገገም ህክምና ጋር በማቀናጀት በሆስፒታሎች እንዲጀመር፣ የሚጥል ህመምን ማከም የሚችሉ ባለሙያዎችን ቁጥር ማብዛት ከማስቻሉም በላይ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን በመቅረጽ፣ በየቤታቸው የሚገኙ ታማሚዎችን ወደ ህክምና ተቋማት የማምጣት፣ የመድሃኒት ተደራሽነትና ክምችት እንዲኖር የማድረግ በርካታ ስራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝም ዶ/ር ደረጄ ተናግረዋል።
መደረግ ስላለበት የመጀመሪያ እርዳታ ሃሳባቸውን የሰጡት የኬር ኢፕሌፕሲ መስራችና ፕሬዚዳንት ወ/ሮ የእናት የውነቱ ታማሚ በወደቀ ጊዜ ከጭንቅላት ስር ለስላሳ ትራስ ነገር ማድረግ፣ ሲንፈራገጥ ራሱን እንዳይጎዳ ማድረግ (እንደ እሳት፣ ኤሌክትሪክና ስለታማ ነገሮችን ማራቅ) እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
አንገት አካባቢ ያሉ የልብስ ቁልፎችን ማላላት፤ መንቀጥቀጡ ከቆመ በኃላ እስኪነቃ ድረስ በጎኑ ማስተኛት፣ ክብሪት አለማሽተት፣ ህመምተኛው እስኪነቃ ድረስ አብሮ መቆየት፣ህመምተኛው ከነቃ በኋላ ማረጋጋትም ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡
እንዲሁም መንቀጥቀጡ ከ 5 ደቂቃ በላይ የሚረዝም ከሆነ ወይንም የታማሚዉ የቆዳ ቀለም ወደ ሰማያዊነት ከተለወጠ በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋም መውሰድ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።