በአፍሪካ ሦስት አህጉራዊ የፋይናንስ ተቋማትን ለማቋቋም የተጀመሩ ጥረቶች ይጠናከራሉ ተባለ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ መሪዎች ሦስት አህጉራዊ የፋይናንስ ተቋማትን ለማቋቋም የተጀመሩ ጥረቶችን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ።
መሪዎቹ ዛሬ ማለዳ ከ37ኛ የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ስብሰባ ጎን ለጎን የዓለም የፋይናንስ ሥርዓትን ለማሻሻል የአፍሪካ አጀንዳን በተመለከተ ምክክር አካሂደዋል።
በአህጉሪቱ የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ባንክና በአፍሪካ ሞኒተሪንግ ፈንድ ለማቋቋም በፈረንጆቹ 2009 እና በ2014 በቅደም ተከተል ሕግ መዘጋጀታቸው ይታወሳል።
ይሁንና የኅብራቱ አባል ሀገራት ሕጉን ባለማጽደቃቸው ወደ ሥራ ሊገቡ አልቻሉም።
እነዚህን ተቋማት ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል በቂ የፋይናንስ ኃብት ባለመሰባሰቡ ተቋማቱን ወደ ሥራ ማስገባት አለመቻሉንም ነው ኅብረቱ የገለጸው።
በተመሳሳይ በፈረንጆቹ በ2006 ደግሞ የፓን አፍሪካ የአክስዮን ገበያ ለማቋቋም የአፍሪካ ኅብረት የዳሰሳ ጥናት እንዲያካሂድ መሪዎቹ ውሳኔ አሳልፈው እንደነበርም አስታውሰዋል።
ይህንንም ተከትሎ በዛሬው ዕለት ስብሰባ ያደረጉት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በአፍሪካ የሞኒታሪ ዞኖችን በማዋሃድ የአፍሪካ የሞኒታሪ ኅብረት ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተለይም የአፍሪካ ማዕከላዊ ባንክ፣ የአፍሪካ ሞኒተሪንግ ፈንድና የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ባንክ ለማቋቋም የተጀመረውን ጥረት ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።