አርማዳ ሆልዲንግ ግሩፕ በኢንዱስትሪ ፓርኮች መዋዕለ-ነዋይ የማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዱባዩ አርማዳ ሆልዲንግ ግሩፕ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ነፃ የንግድ ቀጠና መዋዕለ-ነዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ከግሩፑ ባለቤት መሀመድ ራሂፍ ሀኪሚ (ዶ/ር) ጋር በበይነ መረብ ተወያተዋል።
የሆልዲንግ ግሩፑ ባለቤት ሀኪሚ(ዶ/ር) ኩባንያዎቻቸው የተሰማሩባቸውን የፋርማሲዩቲካል ፤ የግብርና ምርቶች ማቀነባበር እንዲሁም የሪልስቴት እና የአገልግሎት ኢንቨስትመንት ሴክተሮች በኢትዮጵያ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ነፃ ንግድ ቀጠና የማስፋፋትና መዋዕለ-ነዋይ የማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው አክሊሉ ታደሰ÷ ግሩፑ በሚሰማራበት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊ ድጋፎች እንደሚደረጉ ማረጋገጣቸውን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ተቀማጭነቱን በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ያደረገው አርማዳ ሆልዲንግስ ግሩፕ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከ20 የሚበልጡ ኩባንያዎች በስሩ የሚተዳደሩ ሲሆን በፋርማሲዩቲካል፣ በሪልስቴት ግንባታ፣ በኮንትራትና ፋሲሊቲ ማኔጅመንት እንዲሁም በቅንጡ ሆቴሎች ግንባታ የተሰማራ ግዙፍ የኢንቨስትመንት ግሩፕ ነው።