Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል በዓልን ስናከብር በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን ስናከብር በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ፡፡

አፈ ጉባኤው 128ኛውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን አስመልክት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸው፤ የዓድዋ ድል ከሌሎች ድሎች ሁሉ ልቆ ታሪኩ ሳይደበዝዝ ዘመናትን እየተሻገረ የመቀጠሉ ምስጢር የአይቻልምን መንፈስ በመስበር «የሰው ልጅን» እኩልነት በዓለም አደባባይ የመሰከረ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል የተነጣይነትን ስሜት የገደለ፣ የወል እውነትንና አብሮነትን በጽኑ መሠረት ላይ ያኖረ፣ በዘመናዊው ዓለም የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን የኃያልነት እና በተለምዶ እውነት የሚመስለውን የነጭ የበላይነት የሀሰት ትርክት በእውነተኛው የእኩልነት ትርክት የቀየረ የዓለም ጉልህ የታሪክ ክስተት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ድሉ በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ላለፉት 128 ዓመታት የማይዳሰስ ሀውልት ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ይህ የማይዳሰስ ሐውልት በለውጡ መንግሥት ሕያው ሆኗል ብለዋል፡፡

የዓድዋ ታሪክ ታሪኩን በሚመጥን ደረጃ በአፍሪካ መዲና በሆነቸው አዲስ አበባ ሙዚዬም መገንባቱ ትውልዱ ከአባቶቹ ታሪክ ተምሮ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት በመገንባት የራሱን ታሪክ እንዲያስመዘግብ የሚስችል መሆኑም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከአድዋ ድል ሕዝባዊ ፍቅርን፣ ወንድማማችነትንና እህትማማችነት በመማር ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በነጻነት የሚኖርባት ሀገር እንድትሆን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.