Fana: At a Speed of Life!

ሁለት ሲኖ ትራኮች እንዲሰረቁና እንዲሰወሩ አድርገዋል የተባሉ የቀድሞ የፖሊስ አባላት እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለት ሲኖ ትራክ ተሽከርካሪዎች እንዲሰረቁና እንዲሰወሩ አድርገዋል የተባሉ ሶስት የአዲስ አበባ የቀድሞ ፖሊስ አባላትን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች በተከሰሱበት ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ከባድ የሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ብይን ሰጠ።

ችሎቱ በክስ መዝገቡ የተካተቱ ሌሎች ሶስት ተከሳሾችን በሚመለከት ደግሞ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል።

ተከሳሾቹ 1ኛ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአራዳ ክ/ከ አራት ኪሎ ፖሊስ ጣቢያ የቀድሞ የፖሊስ አባልና የወንጀል መከላከል ቡድን መሪ የነበረው ዋና ሳጅን ትግሉ ሰቦቃ፣ 2ኛ እና 3ኛ ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአዲስ ከተማ ክ/ከ ፖሊስ መምሪያ የጊቢ ጥበቃ አባላት የነበሩት ኮ/ብል ዘነበ ኩማ እና ኮ/ብል መንግስቱ እንቻሌ እንዲሁም 4ኛ አቶ ላዕከ ተስፋ ገ/ስላሴ፣ 5ኛ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ውስጥ የቦሌ አራብሳ ፕሮጀክት 13 ጥበቃ የነበረው መልካሙ አያና፣ 6ኛ መላኩ ካላዩ ፣ 7ኛ ከበደ ገ/እየሱስ፣ 8ኛ ወንዶሰን ወይም ኢብራሂም ረጋሳ ገለታ እና 9ኛ ሮቤል ሙሉአለም ሃይሉ ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል በ2015 ዓ.ም በተከሳሾች ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በክስ ዝርዝሩ ላይ እንዳመላከተው፤ ተከሳሾቹ የማይገባቸውን ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በጥቅም በመመሳጠር በዋና እና በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ላይ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ የፖሊስ አባላት ፖሊሳዊ ኃላፊነታቸውን ያለአግባብ በመገልገል በአዲስ አበባ በለሚ ኩራ ክ/ከ ወረዳ 6 ቦሌ አራብሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ቦሌ አራብሳ ሳይት ውስጥ በመግባት በጥበቃ ስራ ላይ የነበረ (የዐቃቤ ሕግ ምስክር) ግለሰብን “ለወንጀል ምርመራ ትፈለጋለህ” በማለት 1ኛ ተከሳሽ ከ3ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን ከጥበቃ ስፍራው ወደ ሌላ ቦታ ወስደዋል።

2ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ደግሞ በቦታው የነበሩ ንብረቶችን እንዲያወጡ በመርዳት 11 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ሁለት ማለትም የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 03-95058 ኢት የሆነ እና የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 03-16409 ኢት የሆኑ ሁለት ሲኖ ትራክ ተሽከርካሪዎችን 6ኛ ተከሳሽ ሞተሩን በካቻቢቴ በማስነሳት ከ9ኛ ተከሳሽ ጋር ተሽከርካሪዎችን ይዘውና ሌሎቹ ደግሞ አጅበው ወደ አዳማ በመውሰድና በመሰወር፣ 8ኛ ተከሳሽ ደግሞ ከሌሎች ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን አንደኛውን ተሽከርካሪ ለግለሰብ በ600 ሺህ ብር በመሸጥና ገንዘቡን በ7ኛ ተከሳሽ ስም በተከፈተ በአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ሂሳብ በማስገባትና በተለያዩ መጠኖች ገንዘቡን መከፋፈላቸው ተጠቅሶ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሰው ነበር።

ከተከሳሾቹ መካከል ስድስቱ ችሎት ቀርበው ክስ ዝርዝሩ የደረሳቸው ሲሆን÷ ቀሪ ሶስት ተከሳሾች ግን በተደጋጋሚ መጥሪያ ተደርጎላቸው ሳይቀርቡ መቅረታቸውን ተከትሎ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ተደርጓል።

ችሎት የቀረቡ ስድስቱ ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምንም ብለው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ ገላጭ ማስረጃዎችን እና ስምንት የሰው ምስክሮችን ቃል አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት 1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾችን በሚመለከት በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ማስረጃ በወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ ና ለ፣ አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና አዋጅን ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 2 መሰረት እንዲከላከሉ በሙሉ ድምጽ ብይን ሰጥቷል።

5ኛ፣ 8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾችን ደግሞ በዚሁ ድንጋጌ ስር በሌሉበት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ተከላከሉ የተባሉ ተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅ ለሚያዚያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠ ሲሆን÷ በዚህ ቀን ዐቃቤ ሕግ የጥፋተኝነት ፍርድ የተላለፈባቸው ሶስት ተከሳሾችን በሚመለከት የቅጣት አስተያየት እንዲያቀርብ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.