ማዕከሉ የሴቶችን እኩልነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ሚና አለው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የሴቶችን እኩልነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ሚና አለው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሕመድ (ዶ/ር) “ለነገዋ” የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ማዕከሉ በችግር ላይ ለሚገኙ ሴቶች አዲስ የህይወት ምዕራፍ እንደሚከፍት ተናግረዋል።
ማዕከሉ የተሻለ ነገን፣ ብሩህ ተስፋን፣ ፅናትና የሰርቶ የመለወጥ እድልን የመትከል ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለሴቶች እኩል ተጠቃሚነት እየተሰሩ ባሉ በርካታ ስራዎች አበረታች ውጤቶችም እየተመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁንም በርካታ ሴቶች ለኢኮኖሚ ጥገኝነትና ለአካላዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ማዕከሉ ሁሉንም ችግሮች የሚፈታ ባይሆንም ለበርካቶች ተስፋ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ለጎዳና ህይወትና ለወሲብ ንግድ የተጋለጡ ሴቶች ራሳቸውን ችለው ወደ ኢኮኖሚ እንዲገቡ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው መሰረት እንደሚጥል አመልክተዋል።
ማዕከሉ በዓመት በአራት ዙሮች ሴቶችን በማሰልጠን በቂ ተሃድሶ አግኝተው ወደ መደበኛ ህይወት እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።