Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር በ29 ወረዳዎች ላይ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተሰራው የህግ ማስከበር ስራ በ29 ወረዳዎች ላይ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አስታውቋል፡፡

የዞኑን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮንን እንደገለፁት፥ ባለፉት 8 ወራት በዞኑ የሰላም፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡

በህግ ማስከበር ስራው ከመከላከያ ሠራዊትና የአካባቢው የፀጥታ ሀይል እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በተሰራው ስራ አንፃራዊ ሰላም መጥቷል ብለዋል።

ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት ወደ 15 ወረዳዎች ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ሆነው እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ አካባቢዎችን ሙሉ ለሙሉ ነፃ በማድረግና የመንግስት መዋቅርን መልሶ በመዘርጋት ህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉን ገልጸዋል።

ሰላምን ከማረጋገጥ ስራ ጎን ለጎን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ በበጋ መስኖ 35 ሺህ ሄክታር ስንዴ ለማልማት ታቅዶ 26 ሺህ ሄክታሩን በዘር መሸፈን መቻሉን በአብነት አንስተዋል።

በተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ስራም በዞኑ 348 ቀበሌ ከ840 ሺህ በላይ አርሶአደሮች በማሳተፍ በ23 ቀናት ውስጥ የተፋሰስ ልማት መሠራቱን ተናግረዋል።

ይህም በብር ሲሰላ ወደ 8 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር እንደሚገመትም ነው አቶ አሊ መኮንን የገለፁት።

የአፈር ማዳበሪያ ስርጭትን በተለመለከተም ዞኑ 501 ሺህ ኩንታል የማሰራጨት እቅድ እንዳለው ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥም 331 ሺህ ኩንታል ለዞኑ ደርሶ 260 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አብራርተዋል።

ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ ተደራሽ የማድረግ ስራው አሁንም የቀጠለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በገቢን ከመሰብሰብ አኳያም 3 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ግብር መሰብሰብ መቻሉን አንስተዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማርገብ ገበያውን ለማረጋጋት ጊዜያዊ መፍትሄ እንዲሆን ዩኒየኖችና ህብረት ስራ ማህበራት 222 ሚሊየን ብር ተዘዋዋሪ ብድር መድበው የግብርናና የኢንዱሰትሪ ምርቶችን እያቀረቡ ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ በደቡብ ወሎ ዞን ሰላምን ለማፅናት ከፀጥታ ስራው ጎን ለጎን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

በዞኑ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ከ316 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ መሆናቸውም ተነግሯል።

በእሌኒ ተሰማና ዓለምሰገድ አሳዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.