የመደመር ሐሳብ የዕይታ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገ መንገድ ነው – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመደመር ሐሳብ በሀገራችን አዲስ የዕይታ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገ ሀገር በቀል መንገድ ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
“የለውጡ ትሩፋቶችና መደመር” በሚል መሪ ሐሳብ በሐረር ከተማ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ሲሆን÷ በመድረኩም የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
አቶ ኦርዲን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግርም÷ የመደመር ሐሳብ በሀገራችን አዲስ የዕይታ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገ ሀገር በቀል መንገድ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የመደመር እሳቤ ሀገርን የሚያፀኑ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባትና የለውጥ ሥራዎችን በትጋት በመሥራት እድገት ያስመዘገብንበት ነውም ብለዋል፡፡
እሳቤው ተጠናክሮ ባህል ሆኖ ለትውልድ እንዲሻገር የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በመድረኩ በመደመር እሳቤ ላይ የተዘጋጁ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገ ሲሆን÷ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተመዘገቡ ለውጦችም ቀርበዋል፡፡
በቲያ ኑሬ