Fana: At a Speed of Life!

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝ ስርዓት በመዘርጋት በችግሩ ልክ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቴክኖሎጂ የተደገፈና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝ ስርዓት በመዘርጋት በችግሩ ልክ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አባሶ ተፈራርመዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል÷ እንደ ሀገር የተቀናጀ የትራፊክ አደጋ መመዝገቢያ የመረጃ ቋት አለመኖሩ በችግሩ ልክ ምላሽ ለመስጠት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ገልጸው፤ ስምምነቱ ይህንን ችግር እንደሚቀርፍ ተናግረዋል፡፡

መረጃዎችን ለማሰባሰብ ጥቅም ላይ የሚውለው መተግበሪያ “አር-ኤ-ዲ-ኤም-ኤስ” እንደሚባል ገልጸው÷ መተግበሪያው በየትኛውም ቦታና ጊዜ የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችን በአንድ ቋት በመያዝ ማሻሻያ ግብዓት ወይም ሌሎች እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ጀማል አባሶ በበኩላቸው÷ አገልግሎቱ የትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝ ስርዓትን ማዘመንን ጨምሮ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናወን መቆየቱን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሀገሪቱን የመንገድ ትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝ ለማዘመን እና ታማኝነት ያለው አሠራር ለመዘርጋት በተጠናው ጥናት መሰረት ከፌደራል ፖሊስ ጋር በትብብር ለመሥራት መስማማታቸውንም ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.