Fana: At a Speed of Life!

ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ለቀሪ ሥራዎች የቤት ሥራ የሰጠ ነው – የአማራ ክልል መንግሥት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ለተከናወኑ የልማት ሥራዎች አድናቆት እና እውቅና ለቀሪ ሥራዎች ደግሞ የቤት ሥራ የሰጠ መሆኑን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ በ96 ከተሞች የተካሄደው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ÷ ሰልፉ መንግሥት ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት ላከናወናቸው የልማት ሥራዎች እውቅና የሰጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሰልፉ ክልሉን ወደ ምስቅልቅል ለማስገባት የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞች የተወገዙበት እና መንግሥት እያከናወነው ያለው ጠንካራ ሕግ የማስከበር ሥራም የተደነቀበት ነው ብለዋል፡፡

ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ለተሠሩት የልማት ሥራዎች አድናቆትና እውቅና፣ ለቀሪ ሥራዎች ደግሞ የቤት ሥራ የሰጠ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በተራማጅ አመራሮች የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን እውቅና ከመስጠቱ በተጨማሪ በቀጣይም ሕዝብን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ ለመንግሥት አመራሩ የቤት ሥራ የሰጠ ነው ብለዋል።

ሕዝቡ በለውጡ የተመለከታቸውን እና ተጠቃሚ የሆነባቸውን የልማት ሥራዎች ተገንዝቦ ያመሰገነበት ሰልፍ እንደሆነም አመላክተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከነበረበት ውስብስብ አፈጻጸም ተላቅቆ በአዲስ አስተሳሰብ እና አሠራር በማለፍ ወደመጨረሻው ምዕራፍ መድረሱ ሕዝብን ያስደሰተ እና በድጋፍ ሰልፉ ላይም ሰፊ አድናቆት እና መልዕክት የተስተጋባበት ነበር ብለዋል።

የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ጽንፈኝነትን እና አክራሪ ብሔርተኝነትን በመታገል ረገድ ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ዋልታ ረገጥ የሆኑ የጽንፈኝነት አስተሳሰቦችን በማረም ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በመገንባቱ ረገድ ሕዝቡ ያለውን ጽኑ ፍላጎት የገለጸበት ሰልፍ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሚደረገው ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተሠርተው እንዲጠናቀቁ እና ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን በትጋት መሠራት እንዳለበት ግንዛቤ የተጨበጠበት ሰልፍ እንደነበርም ገልጸዋል።

በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአማራ ክልል ሕዝብ ለሰላም እና ለልማት ያለውን ቀናኢነት በመገንዘብ ክልሉ ዘላቂ ሰላምና ኅብረ ብሔራዊነት ለመገንባት የሚያደርገውን ትግል እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.