15ኛው የአፋር ሱልጣን አሕመድ አሊሚራህ አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 15ኛው የአፋር ሱልጣን አሕመድ አሊሚራህ አዲስ አበባ ገቡ።
የሱልጣን አሊሚራህ ልጅ የሆኑት 15ኛው የአፋር ሱልጣን አሕመድ የመላው አፋር ሱልጣን የነበሩት ወንድማቸው ሱልጣን ሀንፍሬ አሊሚራህ ማረፋቸውን ተከትሎ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር መሾማቸው ይታወሳል፡፡
የአፋር ሱልጣን መሪዎች በአፋር ሕዝብ ዘንድ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በባህላዊ ስልቶች በዘላቂነት በመፍታት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ይነገራል።
የአፋር ሱልጣን አሕመድ አሊሚራህ ከውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ ዛሬ አዲስ አበባ ሲገቡም÷ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ዘሐራ ሁመድ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር፣ የአፋር ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር እስማኤል አሊስሮ፣ የቀድሞው ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሀሰን አብደላ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።