Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ በአማራ ክልል ለልማት ሥራዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰላም በመስፈኑ ለልማት ሥራዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማሥተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማሥተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ እና የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች÷ በባሕር ዳር ከተማ የተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን፣ የሌማት ትሩፋት እና የልማት ሥራዎች ጎብኝተዋል፡፡

አቶ አደም በጉብኝታቸው ወቅት ባደረጉት ንግግር አሁን ላይ ክልሉ የተሻለ ሰላም ማግኘቱን ገልጸው÷ ይህም ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።

ከክልሉ ጀምሮ የዞን እና የወረዳ አመራሮች የአካባቢያቸውን ሰላም በቁርጠኝነት እያስከበሩ የልማት ሥራዎችንም በከፍተኛ ተነሳሽነት እያከናወኑ እንደሚገኙ ተመልክተናል ሲሉም ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡

በከተማ አሥተዳደሩ የሌማት ትሩፋት ሥራዎች በስፋት እየተሠሩ እንደሚገኙ መመልከታቸውን ጠቅሰው÷ የዓሣ እርባታ፣ ከብት ማድለብ፣ ዶሮ እርባታ እና ሌሎችም የእንስሳት ዘርፍ ሥራዎች በሰፊው መከናወናቸው ሀገሪቱ የያዘችውን የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ አንስተዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደ ሀገር ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው መሆናቸውን ጠቅሰው÷ በአማራ ክልል በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሥራቸውን እያከናወኑ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከአካባቢው አልፎ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ምርቱን በማዳረስና ችግሩን በመፍታት የሌማት ትሩፋት ሥራን ማገዝ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ ምርት ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ለመሆን አቅዶ መሥራት እንደሚያስፈልግም ነው ያስገነዘቡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.