Fana: At a Speed of Life!

ሃላላ ኬላ ሪዞርትና የዝሆን ዳና ሎጅ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ በአግባቡ እናስተዳድራለን – አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃላላ ኬላ ሪዞርት እና የጨበራ ጩርጩራ ዝሆን ዳና ሎጅ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ በአግባቡ እናስተዳድራለን ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አስታወቁ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የተገነቡ ሎጅና ሪዞርቶች ለክልሎች ተላልፈው የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል እንዲያስተዳድራቸው የሚያደርግ ስምምነት በቅርቡ መፈረሙ ይታወቃል።

በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) (ኢ/ር) የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅና የሃላላ ኬላ ሪዞርት የማስተዳደር ውል ተፈራርመዋል።

አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት÷ አየር መንገዱ በረራ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎች ሲያስተዋውቅ መቆየቱን ገልጸዋል።

ከዚህም ባሻገር በሆቴል አገልግሎት ዘርፍ ባለ 5 ኮከብ የሆነውን የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ተገንብቶ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

አየር መንገዱ በገበታ ለሀገር የተገነቡ ሎጅና ሪዞርቶችን በስካይ ላይት ሆቴል ስር እንዲያስተዳድር መደረጉ የሆቴል ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት ምቹ መደላድል እንደፈጠረለት አስረድተዋል።

በዛሬው ዕለትም የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅና የሃላላ ኬላ ሪዞርትን በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ስር በሚጠበቀው የጥራት ደረጃ ለማስተዳደር ውል መፈራረማችን ትልቅ ዕድል ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቱሪዝም መስኩን ለማስፋፋት በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ የጀመራቸውን ስራዎች በሆቴል አገልግሎት ዘርፉም ለመድገም በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል በዘርፉ ያለው ልምድና ተሞክሮ ሪዞርትና ሎጆችን በብቃት እንደሚመራ የሚያስተማምን ነው ብለዋል።

በዚህም ወደ አካባቢው ለሚያቀኑ ጎብኝዎች ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት በመስጠት ከአካባቢው ባለፈ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.