Fana: At a Speed of Life!

ምርጫ ቦርድ የቀድሞ የኢሕአዴግን ንብረት እንዲያጣሩ ሁለት ኦዲተሮችን ሾመ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀድሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢሕአዴግ/ ንብረት እንዲያጣሩ ሁለት ኦዲተሮችን ሾመ፡፡
 
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም ኢሕአዴግ እንዲፈርስ እንዲሁም የቀድሞ ሶስቱ የግንባሩ አባላት ወራሽ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሐት) በስድስት ወር ውስጥ የንብረት ክፍፍል ተጠናቆ እንዲያቀርቡ ክፍፍሉም የሶስት ፓርቲዎች ወራሽ የሆነው ብልፅግና የሃብቱን ሶስት አራተኛ (3/4) በራሱ ህጋዊ እውቅና ያለው ህወሃት አንድ አራተኛ ( ¼) እንዲወስዱ መወሰኑ አስታውሷል፡፡
 
በውሳኔውም ፓርቲዎቹ የጋራ ንብረት አጣሪ ሾመው የባለመብቶችን መብት እንዲጠበቅ እንዲሁም በተገለጸው ቀመር መሰረትም የንብረት ክፍፍሉ እንዲፈጸም ወስኖ አሳውቆ ነበር፡፡
 
በሌላ በኩል የብልጽግና ፓርቲ የንብረት ክፍፍሉ እያንዳንዱ ፓርቲ በተናጠል በነበረው የአባላት ብዛት ላይ የተመሰረተ እንጂ በእኩልነት ሊሆን አይገባም የሚል አቤቱታ መቅረቡን ነው ያመለከተው።
 
ቦርዱ የሃብት ክፍፍሉን የወሰነው የፓርቲው ህገደንብ “ሁሉም ፓርቲዎች በግንባሩ የጋራ ንብረት እኩል የመጠቀም መብት አላቸው” ሲል ያስቀመጠውን መሰረት በማድረግ መሆኑን ገልጾ ሆኖም ግን ብልጽግና ከዚህ የተለየ ውጤት ሊያስከትል የሚችል ማስረጃ ወይም ሰነድ ካለው ለአጣሪው ማቅረብ እንደሚችል ተገልጾለታል ብሏል ቦርዱ፡፡
 
የመፍረስ ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሁለቱም ወገኖች የሚስማሙበት አንድ የጋራ አጣሪ እንዲመርጡ ለማስቻል የተደረገው ጥረት አልተሳካም ነው ያለው፡፡
 
ስለሆነም ቦርዱ ብልጽግና ፓርቲ እና ህወሃት በየበኩላቸው የመረጧቸው አንድ አንድ የሂሳብ አጣሪዎች በጋራ በመሆን የንብረት ማጣራት ስራውን እንዲያከናውኑ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
 
በዚህም ውሳኔ መሰረት የንብረት ማጣራቱን እንዲያደርጉ የተመረጡት ድርጅቶች የጋራ የስራ እቅድ፣ የጊዜ ሰሌዳ፣ ስራውን የሚያከናውኑበት ቦታ፣ ሁኔታ እና የስራ ህግጋት ለቦርዱ እንዲያቀርቡም በደብዳቤ እንደተገለፀላቸው አስታውቋል፡፡
 
የንብረት ማጣራቱ ሂደት ሙሉ ወጪ በፓርቲዎቹ እንደሚሸፈን በመግለፅም ቦርዱ ሂደቱ የሚደርስበትን ደረጃ በየጊዜው ለህዝብ እንደሚገልፅ አስታውቋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.