የኢትዮጵያ የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ማህበር ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የካፒታል ዕቃዎች የፋይናንስ ማህበር በይፋ ተመስርቷል።
በምስረታው ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የማህበሩ መመስረት በኢትዮጵያ ኢንደስትሪያላይዜሽንና የግብርና መካናይዜሽንን በመደገፍ በዘርፉ የተያዙ ሀገራዊ ዕቅዶች እንዲሳኩ የድርሻውን ይወጣል ተብሏል።
የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥማቸውን የሊዝ ፋይናንስ ችግር በተቀናጀ መልኩ ለመፍታትም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንትና የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ዮሃንስ አያሌው (ዶ/ር)፥ ማህበሩ ለካፒታል ፋይናንስ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የማሽነሪ እጥረትን ለመፍታት በጥናት የተደገፈ መፍትሄ የሚሰጥ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
ማህበሩ ሀገራዊ ልማትን የሚያፋጥኑ ተግባራትን በመደገፍ የድርሻውን ይወጣል በማለት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፥ በኢትዮጵያ አንድ የውጭና አምስት ሀገር በቀል የካፒታል ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ ድርጅቶቹ ከ55 በላይ ቅርንጫፍ ከፍተው ለ5 ሺህ ደንበኞች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ያላቸው የካፒታል አቅም ያላቸው ድርጅቶቹ እስካሁን ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ብድር መስጠታቸውን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፥ የሊዝ ፋይናንስ ኢኮኖሚውን ከማነቃቃትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማምጣት አኳያ ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።
የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስ ተቋማት በቂ ባለመሆናቸው ተደራሽነታቸውን ለማስፋት የግል ዘርፉ ጠንካራ ተሳትፎ ያስፈልጋል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አስፋው አበበ፥ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግር መሳካት የካፒታል ዕቃዎች ፋይናንስን ተደራሽ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።