Fana: At a Speed of Life!

እነ ዮሐንስ ቧያለውና ክርስቲያን ታደለ በቀረበባቸው ክስ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እነ ዮሐንስ ቧያለው እና ክርስቲያን ታደለ በቀረበባቸው የሽብር ወንጀል ክስ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠየቁ፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ህገመንግስታዊና በህገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች የሚመለከተው ችሎት በቀጠሮ ተከሳሾች እናቀርባለን ያሉትን የክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅና የማረሚያ ቤት አያያዝን በሚመለከት አቅርበውት የነበረው አቤቱታ ላይ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የማጣሪያ ሪፖርትን ለመጠባበቅ እንዲሁም አቶ ዮሐንስና አቶ ክርስቲያን ከቤተሰብ ጥየቃ፣ ከምግብ አቀራረብ ጋር በተያያዘ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ በችሎቱ የተሰጠው ትዕዛዝ መፈጸምና አለመፈጸሙን ለማረጋገጥ በተሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ችሎቱ ተሰይሞ መዝገቡን ተመልክቷል።

በዛሬው ቀጠሮ ክስ ከተመሰረተባቸው 52 ተከሳሾች መካከል ዮሐንስ ቧያለው፣ ክርስቲያን ታደለ፣ ካሳ ተሻገር (ዶ/ር)፣ መሪጌታ በላይ አዳሙ፣ ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ጨምሮ አጠቃላይ 16 ተከሳሾች ችሎት የቀረቡ ሲሆን ÷ ቀሪ 36 ተከሳሾች ደግሞ ጉዳያቸው በሌሉበት የሚታዩ ናቸው።

ችሎቱ ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ አቶ ዮሐንስ ቧያሌውና ክርስቲያን ታደለ በፍርድ ቤቱ ከምግብና ከቤተሰብ ጥየቃ ጋር ተያይዞ ከሌሎች ታራሚዎች አድሎ ይደረግብናል በማለት ባቀረቡት አቤቱታ መነሻ በማረሚያ ቤት ማስተካከያ እንዲያደርግ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ትዕዛዙ መፈጸሙን ለማረጋገጥ ተከሳሹን ጠይቋል።

አቶ ዮሐንስና አቶ ክርስቲያን ፍርድ ቤቱ ከማረሚያ ቤት አያያዝ ጋር የሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር የሰጠው አግባብነት ያለው ትዕዛዝንና የሄደበት ሂደትን በማመስገን የማረሚያ አስተዳደር የተሰጠው ትዕዛዝን መፈጸሙን ጠቅሰው ፥ በቀጣይም በድጋሚ ተመሳሳይ ተግባር እንዳይፈጸምብን ስጋት አለን በማለት መልስ ሰጥተዋል።

ተከሳሽ መሪጌታ በላይ አዳሙ ባሉበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለጥየቃ የመጣች የ13 አመት ታዳጊ ልጃቸው መታወቂያ አልያዘችም ተብሎ እንዳትገባ መደረጓንና ባለቤታቸው ይዛ የቀረበችው ብሔራዊ መታወቂያ የቀበሌ ካልሆነ አንቀበልም መባሉን ጠቅሰው ፥ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።

49 ተከሳሽ ጋዜጠኛ ዓባይ በምርመራ ወቅት በፖሊስ የተያዙብኝ ንብረቶች ይመለሱልኝ በማለት እንዲሁም የሚደግፋቸው ወላጅ አልባ ሕጻናቶች መኖራቸውን ጠቅሶ ፥ ለመጠየቅ ይፈቀድልኝ በማለት አቤቱታ በቃል አቅርቧል።

ንብረትን በሚመለከት ዐቃቤ ሕግ ኢግዚቪትነት ያልሆኑ ንብረቶች እንደሚመለሱና ኢግዚቪት የሆኑ የተያዙ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ግን ለወንጀል መጠቀሚያ የዋሉና የክሱ አካል ናቸው በማለት እንደማይመለሱ ጠቅሶ መልስ ስጥቷል።

በጠበቆች በኩል ኢግዚቪት በሚል እንደሽፋን ተቆጥሮ የተከሳሽ ንብረቶች ሊያዙ አይገባም በማለት የተከራከሩ ሲሆን ÷ ፍርድ ቤቱም በጉዳዩ ላይ አጣርቶ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጿል።

የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቀደም ሲል በተከሳሾች የቀረበው የማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት አያያዝን በሚመለከት አጣርቶ ሪፖርት እንዲያቀርብ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የደረሰው ግንቦት 8 መሆኑን ከኮሚሽኑ በቀረቡ 3 ተወካዮች ተገልጿል፡፡

በ13 የስራ ቀናቶች በሁለት ከፍሎ ምርመራ ማድረጉን ከኮሚሽኑ የቀረቡ ተወካዮች ለችሎቱ ገልጸዋል።

ይሁንና ከቀረቡ ከህክምናና ሌሎች አቤቱታዎች ጋር ተጨማሪ ማጣሪያ ለማድረግ የአንድ ወር ጊዜ እንዲሰጠው ኮሚሽኑ ጥያቄ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም እስከ ሰኔ 26 ቀን 2016 የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርቱን እንዲያቀርብ ተጨማሪ ቀን ተሰጥቶታል።

ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ዋስትና ህገመንግስታዊ መብት መሆኑን ጠቅሰው ÷ ወ/መ/ስ/ህግ ቁጥር 63 እና 67 መሰረት የተከሰሱበት የሽብር ወንጀል በመሰረታዊነትና በልዩነት ዋስትና ሊያስከለክላቸው አይችልም በማለት ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ጠበቆቹ ተከሳሾቹ ላይ በቀረበ ክስ ላይ 1 ሺህ 100 ሰዎች ሞት በጅምላ መፈጸሙን የተጠቀሰ መሆኑን ገልጸው ፥ ማን ማንን ገደለ የሚል ዝርዝር ስም ባልቀረበበት ሁኔታ ላይ የዋስትና ሊከለከሉ የሚችሉበት አግባብ የለም በማለት የመከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በጠበቆች በኩል የተነሱ የመከራከሪያ ነጥቦች የሕግ መሰረት የሌላቸው ናቸው በማለት የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሞ ተከራክሯል።

ዐቃቤ ሕግ በቀረበባቸው ክስ ዝርዝር የፀጥታ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ ረገድ ተሳትፎ ያላቸው ተከሳሾች አሉ በማለት በተለይም የሰዎችን ሞት በሚመለከት የተሳትፎ ደረጃ መጠቀሱን ገልጾ ፥ ከ15 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ ድንጋጌ ስር በመከሰሳቸው ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም በማለት ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱ የቀረቡ የዋስትና ክርክሩን መርምሮ ተገቢ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው አማካኝነት በቀረበባቸው የሽብር ክስ እንዲሻሻልላቸው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ በሶፍት ኮፒና በጽሁፍ አቅርበዋል።

በቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ ዐቃቤ ሕግ መልስ እንዲሰጥበት በማለት ፍርድ ቤቱ መርምሮ በቀጣይ ቀጠሮ ብይን እንደሚሰጥበት አስታውቋል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.