Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የከተማዋ የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ “በጎ ፈቃደኝነት ለማህበረሰብ ለውጥ” በሚል መሪ ሃሳብ የዝግጅት ትውውቅና የሥራ ስምሪት የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በዚሁ ጊዜ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አብርሃም ታደሰ፥ በየዓመቱ በክረምት ወቅት በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ህይወት ማሻሻል ያስቻሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ለመዲናዋ ነዋሪዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አቅም በሚሆኑበት መልኩ ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በ2016 ዓ.ም የበጋ ወቅት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ3 ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ወገኖች በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውቀዋል።

በዚህም 11 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሚገመት የልማት ስራ በማከናወን የመንግስትን ከፍተኛ ወጪ ማዳን እንደተቻለ አስረድተዋል።

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም 2 ሚሊየን በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ 5 ቢሊየን ብር የሚገመት የልማት ስራ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ለመጪው የክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዐበይትና ንዑሳን መርሐ-ግብሮች ተቀርጸው ተግባራዊ የሚሆኑበት ዝግጅት እንደተጠናቀቀ አስረድተዋል።

አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአረጋውያንና አቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳትና ሌሎች የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል፡፡

በዚሁ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብርም 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዜጎች በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አንስተዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለይም የአቅመ ደካማና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸውን ዜጎች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እየተመዘገበ ያለውን ውጤት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይቆያል ነው የተባለው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.