ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር ተወያይተዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የጤና ዘርፉ የሰው ሃይል ልማት፣ የጤና ፋይናንሲንግ እና መደበኛ የክትባት አገልግሎትን ለማጠናከር የሚወሰዱ እርምጃዎችን እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ድርጅቱ የወባ እና የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶችን እንደሚደግፍ ነው የተገለጸው፡፡
ዶ/ር መቅደስ ዳባ ÷ኢትዮጵያ ሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎትን ለማረጋገጥ እና በቀጣይም የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤን ለማጠናከር ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር እንደምትሰራ ተናግረዋል።
በቀጠናው ጠንካራ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ማዕከል ለመገንባት፣ የድንገተኛ ህክምና ቡድንን ጨምሮ አጠቃላይ የጤናው ዘርፍ የሰው ሃይል ልማትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የትብብር ማዕከል ለማቋቋም እንዲሁም ለአፍሪካ ብሎም ለሌሎች ዓለም ሀገራት የሚተርፍ የሀገር ውስጥ ምርትን ለማዳበር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ የህክምና አገልግሎት ግብዓቶችን ለማምረት ያላት ፍላጎት እና አቅምን በተመለከተም ሰፊ ውይይት መደረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ÷ ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ደንብ ማሻሻያዎች ውስጥ ላሳየችው የነቃ ተሳትፎ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የዓለም ጤና ድርጅት እና ሌሎች ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ አጋር ድርጅቶች የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ጠይቀዋል።