Fana: At a Speed of Life!

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች ላለመግባባት መንስዔ ናቸው – አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ ሐሰተኛና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት እየሆኑ ነው ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ፡፡

የክልሉ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ሕዝባዊ የሰላም ውይይት በኑዌር ዞን ላሬ ወረዳ ተካሂዷል።

ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የሕዝቦችንን የጋራ ዕሴት በማዳበር ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ ይገባል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ የፀጥታ መደፍረስ ማጋጠሙን አንስተው÷ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ ሐሰተኛና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶች በፀጥታ አካላትና በሕብረተሰቡ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም አንዳንድ የጥፋት አካላት የስም ማጥፋት ሥራ ሲሠሩ እንደሚስተዋል በመግለጽ አግባብነት የሌለው ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የስም ማጥፋቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል አንዱ የመከላከያ ሰራዊት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሠራዊቱ ብሔር፣ ሃይማኖት እንዲሁም በአካባቢ የታጠረ አለመሆኑን ሕብረተሰቡ ሊገነዘብ ይባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የ104ኛ የራስ ዳሽን ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አበባው መንግስቱ በበኩላቸው÷ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በክልሉ የፀጥታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ሠራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበር እያስጠበቀ እንደሆነ ሕዝቡ ሊያውቀው ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ከኑዌር ዞን ከአምስቱ ወረዳዎች እና ከኢታንግ ልዩ ወረዳ የተወከሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.